የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በዩኒሴፍ ዓለም አቀፍ የተዘጋጀውን ዩ ሪፖርት (U- Report) የወጣቶች አጭር የጽሁፍ መልዕክት በነጻ ለመላክ የሚያስችል ስምምነት መስማማቱን አስታውቋል፡፡
ስምምነቱም የስርዓቱ አባል የሆኑ ወጣቶች ለአንድ ዓመት ያለክፍያ መልዕክት እንዲደርሳቸው የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
በዩኒሴፍ ዓለምአቀፍ የተዘጋጀው ዩ ሪፖርት የወጣቶች መልዕክት መለዋወጫ ስርዓት፤ ወጣቶች ለአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠትና ድጋፍ ማድረግ የመሳሰሉ የማህበራዊ እድገትን የሚያመጡ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ግንዛቤ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በ99 አገሮች ከ36 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ስርዓቱ፤ በወጣቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያም በ2016 ዓ.ም ጥር ወር ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ እስካሁን ከ17 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሉት ተገልጿል።
ይህ ስምምነት በትምህርት፣ በጤና እና ማህበራዊ እድገት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን ለማሰራጨት እድል የሚሰጥ ሲሆን፤ የዘመናዊ ስልክ የሌላቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተነግሯል።
ይሄውም የነጻ መልዕክቱ የዲጂታል ልዩነቱን የሚፈታ ሆኖ በተለይ በገጠራማ አከባቢ ያሉ ወጣቶችን በውሳኔ ሰጪነት ላይ እንዲሳተፉ መረጃ የማዳረስና የማሳወቅ እድሎችን እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው።
ሳፋሪኮም የኢትዮጵያ ደንበኞቹ 8 ሚሊዮን መድረሳቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ ከሀገሪቱ ሕዝብ ግማሹን መድረስ የሚያስችል ኔትወርክ መዘርጋቱንም ገልጿል።
በተጨማሪም የ4G ኔትወርክ አገልግሎቱን በማስፋት የማህበረሰቡን እድገት፣ ወጣቶችን ማብቃት እና የዲጂታል ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን እንደሚደግፍ አስታውቋል።
በዚህም የዜሮ ክፍያ እድል በመስጠት ዩ ሪፖርት ላይ ያሉ ወጣቶቻችን እንዲሳተፉ፣ መረጃ እንዲያገኙ እና ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ ገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ