በጎርጎሮሳውያኑ 1937 ራስ ደስታ ዳምጠው በተያዙበት ወቅት በስፍራው በነበረ የጣልያን ወታደር ተወስዷል የተባለው ይህ የወርቅ ሜዳልያ፤ 'ላይቭኦክሽነርስ' በተሰኘ የድረ-ገጽ ላይ ለጨረታ ከቀረቡ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ ተነግሯል፡፡
በዚህም የኮከብ ቅርጽ ያለው የወርቅ ሜዳሊያ ከ60 ሺሕ እና 90 ሺሕ ዩሮ መካከል ግምታዊ ዋጋ ተሰጥቶታል።
በአሜሪካን ሀገር የሚኖሩት እና የራስ ደስታ ዳምጠው የልጅ ልጅ የሆኑት አማሃ ካሳ “ከአያታችን አስከሬን ላይ የተወሰደ ሜዳሊያ ነው" ያሉ ሲሆን፤ በጨረታ ካታሎጉ ላይ ያለውን ጽሑፍ ማንበባችን "ደማችን እንዲፈላ አድርጓል" ማለታቸውን ዘ አርት ጋዜጣ ስለ ቅርሱ በሰራው ዘገባ አመላክቷል።
የራስ ደስታ የልጅ ልጆቹ ሜዳልያው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዝየም እንደሰሚጥ ተስፋ እንደሚያደርጉም መናገራቸው ተመላክቷል።
ትኩረቱን በተሰረቁ ቅርሶች እና ልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎች ላይ አድርጎ በሚንቀሳቀሰው 'አርት ሪከቨሪ ኢንተርናሽናል' በበኩሉ ሜዳሊያውን ለኢትዮጵያ ሙዚየም ተላልፎ እንዲሰጥ ፍላጎት ቢኖረውም፤ ነገር ግን የጨረታው ቤት እቃውን ለማንሳት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ከጨረታው በፊት ለጨረታ ቤቱ በፃፉት ደብዳቤ ሽያጩ እንዲሰረዝ እና ይህ የተዘረፈ ጠቃሚ ቅርስ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ መጠየቃቸውም ተነግሯል፡፡
ራስ ደስታ ዳምጠው በጣልያን ዳግም ወረራ ወቅት በአርበኝነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ በፋሽስት ወረራ ወቅት የሲዳማን ጦር በመምራት ታግለውና አታግለው በጀግንነት አልፈዋል።
እኚህ ጀግና የሀገር ባለውለታ በሥማቸው በአዲስ አበባ ሆስፒታል እንደተሰየመላቸውም ይታወቃል።
በተመሳሳይ በተያዘው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ እ.ኤ.አ 1868 በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተወሰደው የአጼ ቴዎድሮስ ያጌጠ ጥንታዊ ጋሻ፤ ከብሪታኒያው አንደርሰን እና ጋርላንድ የጨረታ ቤት ጨረታው ተሰርዞ፤ ከ156 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ይታወሳል።