የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ ሕገወጥ ነዳጁ ቢፍቱ በሚባል ካምፓኒ በኩል ሲዘዋወር መቆየቱንና ከ 3 ቀን በፊት ለሊት ዱከም ከተማ ላይ በበርሜል ሲቀዳ መያዙን ለአሐዱ ገልጸዋል።
አክለውም፤ "ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድና መቀዳት ካለበት በላይ በመቅዳቱ እንዲሁም ለምን አላማ እንደሚውል የማናውቅ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ውሏል" ብለዋል።
ምክትል ኃላፊው በኦሮሚያ ክልል በ2017 የመጀመሪያው በጀት ዓመት እስከ ትላንትናው ዕለት ድረስ በአጠቃላይ 133 ሺሕ 857 ሊትር ግምቱ 13 ሚሊዮን 781 ሺሕ 423 ብር የሆነ ሕገወጥ ነዳጅ በቁጥጥር ሥር ውሎ፤ 1 ሚሊዮን 559 ሺሕ 11 ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ለአሐዱ ተናግረዋል።
የተያዘው ሕገወጥ ነዳጅ መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ ምን ያክል መጠን እንደያዘ ተለክቶ በመታሸጉ ምን እናድርገው? በሚል ውይይት ተካሂዶ ዛሬ ጠዋት ለነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን እንዳስታወቁ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት "ወደ ዲፖ እንዲገባ አልያም እነሱ በሚያስቀምጡልን አቅጣጫ መሰረት በመሄድ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድበት እየተሰራ ነው" ብለዋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሀረላ አብደላሂ ሕገወጥ ነዳጁን የኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ዛሬ መረጃው እንዳደረሷቸው ገልጸው፤ ከሁለቱ የነዳጅ ቦቴ አንደኛው የቤንዚን ሲሆን ሌላኛው የናፍጣ እንደሆነ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ነዳጅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚዘውር ትልቅ ጉዳይ በመሆኑ በተለይም ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በኋላ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ጠቅሰው ፣ "ማንም ግለሰብ ተነስቶ የነዳጅ ነጋዴ መሆን አይችልም" ሲሉ አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሁለት ሕገወጥ የነዳጅ ቦቴዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ
ሕዳር 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ሁለት ሙሉ የነዳጅ ቦቴ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ አስታውቋል።