የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ ቀደም በ2 ሺሕ 200 ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በአሁኑ ሰዓት ከ1 ሺሕ 250 እስከ 1 ሺሕ 300 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሥራ ላይ የነበረውን የሲሚንቶ መመሪያ ቁጥር 960/2015 ከጥቅምት 29/2017 ዓ.ም ጀምሮ የአሰራር ማሻሻያ መደረጉን ያነሱት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገር ውስጥ ንግድና የሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሊቁ በነበሩ፤ በዚሁ አግባብም ተግባራዊ እንዲሆን የሚመለከተው አካል እንዲያውቀው ስለመደረጉ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ማሻሻያው ከመደረጉ በፊት ይሸጥ ከነበረበት 2 ሺሕ 200 ብር የአንድ ኩንታል ዋጋ ወደ 1 ሺሕ 250 እስከ 1 ሺሕ 300 ብር እንዲወርድ በማድረግ ገበያው መረጋጋቱን አስታውቀዋል።
"ይህ እርምጃ በሲሚንቶ ግብይት ትልቅ ለውጥ ያመጣ እና ውጤታማ የአሰራር ስርዓት ነው" በማለት፤ የሀገር ውስጥ ንግድና የሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
አሐዱም በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሲሚንቶ መሸጫ ሱቆችን ተዘዋውሮ በማየት የሲሚንቶ ዋጋ አሁን ላይ በተጠቀሰው መጠን እየተሸጠ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችሏል።
በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሕግ ውጪ በሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት ላይ ቁጥጥርን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ በ2017 በጀት ዓመት 6 ወር ውስጥ በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ በተደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከ108 ሺሕ በላይ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን መግለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት አማራጭ ገበያዎችን ከማስፋፋት አንፃር፤ በስድስት ወራት ውስጥ 57 አዳዲስ የሰንበት ገበያዎች የተመቻቹ ስለመሆኑና በአጠቃላይ 1 ሺሕ 213 የሰንበት ገበያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ከ2 ሺሕ 200 ብር ወደ 1 ሺሕ 250 ብር መውረዱ ተገለጸ
