የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ በኮንትሮባንድ መድኃኒት ስርጭቱ ውስጥ የግል ፋርማሲዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ተብሏል።

የመንግሥት የመድኃኒት መሸጫ (ፋርማሲዎችም) እንዲሁ ነጻ መድሃኒቶች እና በመንግሥት ሴክተር ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶች፤ ወደ ግል ሻጮች እንዲዘዋወሩ እየተደረገ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የጤና እና ጤና ሃብት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሶንኮ፤ በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ንግድ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ሲሆኑ 67 ሚሊየን ብር የሚገመት ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች በቁጥጥር ሥር ዉሏል ብለዋል።

በዚህም በሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር እና ሽያጭ ላይ የተሳተፉ ከ200 በላይ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት፣ ፍቃድ የመሰረዝና ፍርድ ቤት የማቅረብ ሥራ መሰራቱ ተነግሯል፡፡

ከተለያዩ ዘርፍ የተውጣጡ የመንግሥት ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች እና የጸጥታ አካላት የተሰረቁ መድኃኒቶችን ሲሸጡ መያዛቸውን ተናግረዋል።

"ከመንግሥት ተቋማት፣ ከባለሙያ እስከ የደህንነት ኃላፊዎች የስርቆት ወንጀል ፈፅመዉ ሲሸጡ የተያዙ መሆኑንና እነዚህ የተዘረፉ የመንግሥት ተቋማት ኦዲት እየተደረጉ ነው" ሲሉ ነው አቶ ዮሴፍ የገለጹት።

አክለውም መድኃኒት ቁጥጥር በሚደረግበት ጊዜ በአንዳንድ ቦታዎች በመሳሪያ ጭምር ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩ እንዳለ ሆኖ በክልሉ የሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመቆጣጠር እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ኃላፊው፤ "ሕዝባዊ ትብብርን እንፈልጋን" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ