የካቲት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጽም አሰፋ (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ቅድሚያ በሚሳጣቸው ፖሊሲዎች እና በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በኢትዮጵያ ስላለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የገበያ እድሎች እንደሚወያዩ ተመላክቷል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር እ.ኤ.አ በ2019 የተቋሙ ኃላፊ ከሆኑ በኋላ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ