የካቲት 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ውስጥ የፕላስቲክ ከረጢት ወይም "ፌስታል" በሚል የሚታወቁ የፋብሪካ ምርቶችን መጠቀም፣ ማምረት ብሎም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን የሚከለክል ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወቃል።

ረቂቅ ሕጉ የፕላስቲክ ምርቶች የሚያደርሱትን ዘርፈ ብዙ የጤና፣ የአካባቢ ብክለት፣ የንጽሕናና መሠል ተያያዥ ችግሮች ለማስቀረት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የፕላስቲክ ምርቶች በአካባቢ ላይ ብሎም በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ብዙ በመሆኑ ስስ የፌስታል ምርቶች እንዳይመረቱ መከልከሉን ገልጿል።

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ቡድን መሪ ሰናይት ተስፋዬ፤ የፕላስቲክ ምርቶች በአፈር ውስጥ ተቅበረው በመቶ ዓመታት የማይበሰብሱ ከመሆናቸው ባሻገር በአፈር ውስጥ በቂ አየር እንዳይዘዋወር እና ምርት እንዳይኖር የሚያድጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በፕላስቲክ ምርቶች ውስጥ የሚገኘው 'ፒቢሲ' የተሰኘው ንጥረ ነገር በጥናት ባይረጋገጥም ሙቀት ሲነካው በመትነን ዜጎችን ለካንሰር በሽታ የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፕላስቲክ ምርቶች የሚያደርሱት ጉዳት በተመለከተ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሰፊ ንቅናቄ እየሰራበት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ "የውፍረት መጠናቸው ከፍ ያለ ረዘም ላለ ጊዜ ማገልገል የሚችሉ የፕላስቲክ ምርቶች እንዲመረቱ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

በዚህ መስፈርት ለመስራት በርካታ ፈቃድ የጠየቁ አምራቾች መኖራቸውን አንስተው፤ ከተቀመጠው የፕላስቲክ ደረጃ በታች ያመረቱ በርካታ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን እና ደረጃውን ጠብቀው እንዲያመርቱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ምክክር የተደረገበትና ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የተመራው ረቂቅ ሕግ፤ "ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ" የሚከለክል ነው።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ