የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግሥት የባህር በር በጋራ ለመጠቀም እንዲሁም አንዳቸው የሌላውን ሉዓላዊነት፣ ነፃነት፣ እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ መስማማታቸውን ተከትሎ፤ በቱርክ አሸማጋይነት የሚያደርጉት "ቴክኒካዊ ድርድር" ዛሬ በአንካራ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አሸማጋይነት በታሕሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ያካሄዱት ድርድር ሁለቱንም አገራት በሚያግባባ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተገናኝተው መክረዋል።

በውይይታቸውም ሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የጸጥታ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሰረት የአንካራው ድርድር አካል የሆነው የመጀመሪያ ዙር "ቴክኒካዊ ውይይት" በዛሬው ዕለት በአንካራ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሶማሊያ የማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ ሰኞ ወደ አንካራ ማቅናቱ ተገልጿል።

ሚኒስትሩ የሁለቱን ሀገራት የመጀመሪያ ዙር ቴክኒካዊ ውይይት ለማስጀመር በአንካራ የሶማሊያ ልዑካንን መቀላቀላቸውን በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡

አክለውም "ውይይቱ የአንካራ ቃል ኪዳንን ተግባራዊ ለማድረግ መንገዶች ለማፈላለግ ያለመ" መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአንካራ በተደረስው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና እና ቀጣይነት ያለው የባህር በር መዳረሻ ተጠቃሚነት እንዲኖራት ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ ይህም በሶማሊያ መንግሥት ስልጣን ሥር የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።

ለዚህም የሚሆን የኮንትራንትና የሊዝ ውልን ጨምሮ ሌሎች ሞዳሊቲዎች ላይ በቀጣይ በቅርበት አብረው ለመስራትና ለማጠናቀቅ መስማማታቸው በወቅቱ ተገልጿል።

ይህንን ስምምነት ለማስፈጸምም ከመጋቢት ወር 2017 በፊት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የማመቻቸት ሥራ ይሰራል ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ በ4 ወራት ውስጥ ደግሞ ሂደቱ ተጠናቆ ስምምነት እንደሚፈረም ተመላክቷል።

በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካል ውይይት ዛሬ እንደሚጀመር ነው የተነገረው፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይ ላይ በአንካራ ለተደረሰው የጋራ ስምምነትም በወዳጅነት እና በአጋርነት መንፈስ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ዳግመኛ አረጋግጠዋል።

በስምምነቱ የተቀመጡ የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን በወቅቱ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ