የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዱር እንስሳቶች ከመጠለያ ጣቢዎች እየወጡ ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፤ በየቦታው የዱር እንስሳት ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት አስመልክቶ የሚቀርብ አቤቱዎች በእጅጉን እየጨመሩ መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል።

በቅርብ ጊዜ በተጠና ጥናት መሰረትም አዲስ አበባን ጨምሮ በአጠቃላይ እንደ ሀገርም የተለያዩ የዱር እንስሳት ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እየተባባሰ መሆኑን በማንሳት፤ "ለዚህም ዋነኛ ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዱር እንስሳቱ መኖሪያቸው በመነካቱ ነው" ብለዋል።

ሕገወጥ ሰፈራ፣ አደንና እርሻ እንዲሁም ያልተቀናጀ የኢንቨስትመንት ሥራና መሰል እንቅስቃሴ በመኖሩ እነዚህ ሁሉ ተዳምረው የመኖሪያ አካባቢያቸው በመነካቱ፤ ከቦታው ለቀው በመውጣት ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በመሆኑም ይሄንን ችግር ለመፍታት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ካሉ አመራሮች ጋር በመሆን እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ