የካቲት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጅቡቲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ የሱፍ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል።

ማሕሙድ አሊ የሱፍ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር እንዲሆኑ 33 ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ነው የተነገረው።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለኮሚሽነርነት የተመረጡት የኬንያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያ ማንድራቶን በማሸነፍ ነው።

በዚህም መሠረት ላለፉት ስምንት ዓመታት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የነበሩትን ሙሳ ፋኪ ማኅማትን የተኩት የ59 ዓመቱ ማሕሙድ አሊ ይሱፍ፤ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ኮሚሽኑን የሚመሩ ይሆናል።

በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ፤ የሕብረቱ ሊቀመንበር የነበሩት የሞሪታኒያው ፕሬዝዳንት ሞሃምድ ኡልድ ጋዝዋኒ የሕብረቱ ሊቀ-መንበር ሆነው ለተመረጡት የአንጎላ ፕሬዝዳንት ዧ ማኑኤል ጎሳዌስ ሎሬንሶ ሊቀመንበርነቱን ማስረከባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ