የካቲት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የምትፈልገውን ውክልና እንድታገኝ እንሰራለን ሲሉ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ገለጹ።

ዋና ጸሀፊው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "የተመድና የአፍሪካ ሕብረት ግንኙነትን ሊጠናር ይገባል" ብለዋል፡፡

"ተመድ በማንኛውም ሁኔታዎች ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያለውን ግንኙት ለማጠናከር በሩ ክፍት ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ እስካሁን ድረስ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ ተወካይ የሌላት መሆኑን ገልጸው፤ "ከአፍሪካ ሕብረትና አባል ሀገራት ጋር በመሆን አፍሪካ የምትፈልገውን ውክልና እንዲታገኝ እንሰራለን" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ የጸጥታው ምክር ቤት አባል እንዲኖራት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

"አፍሪካ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ፍትሃዊ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲታገኝ ጥረት ይደረጋል" ሲሉም አስረድተዋል፡፡

"የዘንድሮው ጉባኤ አፍሪካ በቅኝ ግዛት የደረሰባትን ጫና መከስ እንዳለባት ለሌላው ዓለም የምታንጸባርቅበት ነው" ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አፍሪካ ካላት የሕዝብ ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ በመሆኑ፤ ያላትን የሰው ኃይል በአግባቡ ልትጠቀምበት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ጠዋት በተካሄደው በሕብረቱ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ የተሳተፉ አንቶንዮ ጉተሬዝ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ "በአፍሪካ ሰላምን እና ደህንነትን ለማረጋገጥ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በትብብር ሊሰራበት የሚገባ አጀንዳ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"አፍሪካ በአሁን ወቅት ለየት ያሉ ችግሮች እያጋጠሟት ነው" ያሉም ሲሆን፤ ሥር የሰደደው ቀኝ ግዛት፣ የባሪያ ንግድና ሌሎችም ኢ-ፍትሐዊ አሰራሮች በአፍሪካ ላይ ጠባሳ ጥሎ ማለፋቸውን ተናግረዋል።

አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነት እንድታገኝ ጥረት እንደሚደረግም አንስተዋል።

"የዓለም አቀፉ የኢኮኖሚና ፋይናንስ መዋቅር አፍሪካን ያማከለ አይደለም። ኢ-ፍትሐዊ አሰራሮችን ማስተካከል ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ የሚያሰጥ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአሁኑ ውይይት በአራት ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥ ያነሱት ዋና ጸሀፊው፤ ልማትን በማፋጠን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለሳካት ዓለም አቀፉ የፋይናንስ መዋቅር አፍሪካን በማከለ መልኩ ሪፎርም እንዲያደርጉ ግፊት ማድረግ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው ፍትህን በማረጋገጥ በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ምዕራባዊያን ያላቸውን አሉታዊ አተያይ መቀየር መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም በቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የአፍሪካውያንን ተጠቃሚነት ማጎልበት እና በመላው አፍሪካ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በትላንትናው ዕለት በኮንጎ ሪፐብሊክና በሱዳን ከሚስተዋለው ግጭት ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ደህንነት ምክር ቤት ጉባኤ ላይ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

"በሱዳን ካለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ጀምሮ ባለው ግጭት የንፁሃን ግድያ፣ የጾታዊ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተስተዋለ ነው" ያሉት አንቶንዮ ጉተሬዝ፤ ይህም ለቀጠናው ስጋት መሆኑን መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

አክለውም "ለግጭቶች ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሔ የለም ያለንበት ጊዜ የመሳሪያን ድምፅ የሚወገድበት የዲፕሎማሲና የውይይት ነው" ብለዋል።

መግለጫቸውን ሲያጠናቅቁም በሁሉም ሁኔታዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአፍሪካውያን ጋር መሆኑን አስገንዝበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ