ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት 'በምክክር ሂደት ውስጥ ሊካተቱ ይገባሉ' ያላቸውንና ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት አስረክቧል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን የሚመለከቱ 79 አጀንዳዎች መቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት ከአካሄደ በኃላ 'ዋና አጀንዳ ናቸው' ያላቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማስረከቡን አስታውቋል፡፡

የሕዝብ ሚዲያ አስተዳደርን፣ የመረጃ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብት፣ ስርጭት እና ተደራሽነት፣ የፋይናንስ ዘላቂነት እና የማስታወቂያ ፍትሃዊነት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የሚዲያ መሠረተ ልማት፣ የጋዜጠኞች ጥበቃ እና ደህንነትና ዋስትና በአጀንዳነት ተለይተው ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማስረከቡን አስታውቋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን አጀንዳዎቻቸውን ለውይይት ከማቅረብ ባለፈ የሀገሪቱ ችግሮች ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲፈቱና ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምህዳሯን ወደ ጠንካራ፣ ገለልተኛ እና ዲሞክራሲያዊ ተቋምነት እንዲጓዝ ለማድረግ ሊተጉ ይገባል ሲል ምክር ቤቱ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ሰፊ እና ዘርፈ ብዙ ሃሳቦች፣ የአሰራር ሂደቶች፣ የይሁንታ ሃሳቦችን ከፖሊሲ አውጭዎች፣ ሕግ አስፈፃሚዎች እና ሕግ ተርጓሚዎች እንዲሁም፤ ከሕዝቡ የሚፈልጉ እና በዜጎች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ውስጥ የራሳቸው ሰፊ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ በአፅንኦት ሊታዩ ይገባል ተብሏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ