ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ2017 ዓ.ም ስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የደረሱ የ103 የእሳት ቃጠሎ መንስኤዎችን በፎረንሲክ ምርመራ አጣርቶ ውጤቱን ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ዲፓርትመንት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ዘመኑ ያፈራቸውን ዘመናዊ የላብራቶሪ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የቀረቡለትን የእሳት አደጋ ቃጠሎ መንስኤዎችን በማጣራት የደረሰበትን የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት አቅርቧል።

Post image


በዚህም መሰረት፡-
1. በኤሌክትሪክ ቴክኒክ ችግር ምክንያት የደረሰ 50 ቃጠሎ፤

2. በመካኒካል ችግር ምክንያት የደረሰ 11 ቃጠሎ፤

3. ሆን ተብሎ በሰው አማካኝነት የደረሰ 10 ቃጠሎ፣

4. በቸልተኝነት የደረሰ 17 እና

5. በሌሎች ምክንያቶች የደረሰ 15 ቃጠሎ መሆናቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 96 እና በክልሎች ደግሞ ሰባት በአጠቃላይ እንደ ሀገር 103 የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች ደርሰው የአደጋ መንስኤዎችን ማጣራቱን ጨምሮ ገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ "ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሸማ ተራ ነባር የገበያ ማዕከልና በአካባቢው የደረሰው የእሳት አደጋ መንስኤም በኤሌክትሪክ ቴክኒክ ችግር የተከሰተ አደጋ መሆኑን በፎረንሲክ ምርመራ ማጣራት ችያለሁ" ብሏል ፌደራል ፖሊስ።

Post image

በግማሽ ዓመቱ በ582 መኖሪያ ቤት፣ በ12 ተሽከርካሪዎች፣ በ1965 ንግድ ቤቶች፣ በስድስት ፋብሪካዎችና የተለያዩ ድርጅቶች በቃጠሎ ምክንያት ጉዳት ስለመድረሱም የስድስት ወራቱ ሪፖርት አመላክቷል።

ኅብረተሰቡ ቃጠሎ ከደረሰ በኋላ ማስረጃዎች ሳይነካኩ መጠበቅና ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት እንዲሁም፤ የቃጠሎ መንስኤዎች በሙያዊ ምርመራ እስካልተረጋገጡ ድረስ አስተያየት መስጠትና መፈረጅ ፍትሕን እንደሚያዛባ ተገንዝቦ ለፍትሕ መረጋገጥ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ