የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 መብራት ኮንደሚኒየም መግቢያ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች፤ ለመንገድ ግንባታ ተብሎ ከፈረሰው መንገድ ሥር የሚወጣው አፈር ከ3 ዓመት በላይ አስፋልቱ ላይ እየተደፋ ባለመነሳቱ ለመንቀሳቀስ ተግዳሮት ሆኖብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ አካባቢው የቆሻሻ ማከማቻ እንደሆነ አንስተው፤ "ቦታው የንግድ ሥራ የሚሰራበት በመሆኑ ለእንቅስቃሴ እንቅፋት ሆኖብናል። በሚፈለገው ልክ ሥራችንን መስራት አልቻልንም" ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

"ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሆኗል" ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

አሐዱም የነዋሪዎችን ቅሬታ በመያዝ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን አነጋግሯል።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን በሰጡት ምላሽ፤ "በአካባቢው የሚሰራው የመንገድ ግንባታ በመጓተቱ ምክንያት ህብረተሰቡ እየደረሰበት ያለውን እንግልት ባለስልጣኑ የሚረዳው ነው" በማለት ችግሩ እንዳለ አምነዋል፡፡

በቅርቡም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ በመፍጠር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ የማስተካከያ ሥራዎችን ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Post image

በመሆኑም የሚታዩ ችግሮች በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ብቻ ሊፈቱ የማይችሉና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚያስፈልገው በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታ ሊዘገይ እንደሚችል የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ይህንን ጉዳይ ህብረተሰቡ ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ነዋሪዎች ቅሬታ ያቀረቡበትን ፕሮጀክት በሚመለከት ግን የማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደው የተጓተተው የመንገድ ግንባታን ለማጠናቀቅ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቁ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ