የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደሀገራቸው በሚገቡ በሁሉም የብረታ ብረት እና የአሉሚኒየም ምርቶች ላይ አዲስ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።
ትራምፕ ትናንት በኒው ኦርሊየንስ በተካሄደው የኤን ኤፍ ኤል ሱፐር ቦውል ላይ በተገኙበት ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፤ ዛሬ ሰኞ አዲሱን የብረታ ብረት እና የአሉሚኒየም ታሪፍ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አክለውም በአሜሪካ ምርቶች ላይ ቀረጥ የጣሉ ሁሉም ሀገራት ላይ በቅርቡ ተመሳሳይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ የገለጹ ሲሆን፤ "ይህንንም ማክሰኞ ወይም ረቡዕ አሳውቃለሁ" ብለዋል።
"በጣም በቀላሉ፣ የሚያስከፍሉን ከሆነ እኛም እናስከፍላቸዋለን" ሲሉም፤ ትራምፕ ስለ አጸፋዊ ታሪፍ ያላቸውን እቅድ ለጋዜጠኖች አስታውቀዋል።
የአሜሪካ መንግሥት እና በየብረታ ብረት ኢንስቲትዩት መረጃ መሠረት፤ ካናዳ፣ ብራዚል እና ሜክሲኮ ትላልቆቹ የአሜሪካ የብረታ ብረት ምርት ምንጮች ሲሆኑ፤ ደቡብ ኮሪያ እና ቬትናም እነዚህን ሀገራት ይከተላሉ።
በሃይድሮ ፓወር የበለጸገችው ካናዳ የአሉሚኒየም ብረትን ለአሜሪካ አቅራቢ ዋና ሀገር ስትሆን፤ በዚህም በ2024 የመጀመሪያዎቹ 11 ወራት ውስጥ ከሀገሪቱ የውጪ ንግድ ጠቅላላ ገቢ 79 በመቶውን ይሸፍናል።
የካናዳ የኢኖቬሽን፣ ሳይንስ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ፍራንኮይስ ፊሊፕ ሻምፓኝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "የካናዳ ብረት እና አልሙኒየም ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች በአሜሪካ ውስጥ ከመከላከያ፣ ከመርከብ ግንባታ እና ከአውቶሞቢል ድጋፍ ሰጪ ናቸው።" ብለዋል፡፡
አክለውም፤ "ለካናዳ፣ ለሠራተኞቻችንና ለኢንዱስትሪዎቻችን መቆማችንን እንቀጥላለን።" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ትራምፕ የአሜሪካ መንግሥት የጃፓኑን 'ኒፖን ስቲል' በሀገሪቱ ኢንቨስት እንዲያደግ ግፊት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ፣ ነገር ግን ኩባንያው የአብዛኛው ድርሻ ባለቤት እንዲሆን እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

ጃፓን ‘ኒፖን ስቲል’ የተሰኘውና በፒትስበርግ የሚገኘውን የብረት ማምረቻ 15 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ያቀረበችው ሀሳብ ተከትሎ፤ ሁለቱ ሀገራት ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የጃፓኑ ጠቅላይ ምኒስትር ሺጌሩ ኢሺባ ከትናንት በስተያ በዋይት ኀውስ ተገኝተው ከትራምፕ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በተለያዩ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም ውይይታቸው ላይ ዶናልድ ትራምፕ የብረት ማምረቻው ለአሜሪካ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ ፋብሪካውን ከመግዛት ይልቅ ሌላ መዋዕለ ነዋይ መድበው እንዲሰሩ ሃሳብ ማቅረባቸው ተመላክቷል።
'ኒፖን ስቲል' በዚህ የትራምፕ ሃሳብ ላይ እስከአሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሁለተኛውን የስልጣን ዘመናቸውን የተለያዩ ትላልቅ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የጀመሩት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በካናዳ፣ በሚክሲኮ እና በአውሮፓ ህብረት ላይ 25 በመቶ በብረት እንዲሁም 10 በመቶ በአልሙኒየም ምርት ላይ ታሪፍ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ነገር ግን ከካናዳ እና ሜክሲኮ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ፤ በሀገራቱ ላይ ጥለውት የነበረውን ታሪፍ ለአንድ ወር አራዝመውታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ