የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከኢትዮጵያ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ውስጥ አንዱ እና በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘው የዋልያ አይቤክስ በተለያዩ ጊዜያት በሚስተዋሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ህልውናው ለአደጋ እንዲጋለጥ መዳረጉን የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የዋልያ አይቤክስን ህልውና ለመታደግ እና ዘላቂነት ባለመው መንገድ ለመጠበቅ ብሔራዊ የጥበቃ ስትራቴጂ ማዘጋጀት በማስፈለጉ፤ ባለስልጣኑ ከአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላትን ያሳተፈ ውይይት በጎንደር ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፤ የዱር እንሰሳት ሀብት መጠበቅ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ የሆነው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሕልውና በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች የአደጋ ሥጋት ተጋላጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ሰለሞን አያይዘውም በብሔራዊ ፓርኩ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመከላከል አህጉራዊ፣ ቀጣናዊ፣ ብሔራዊና አካባቢያዊ ትብብርና አጋርነት እንዲሁም የሁሉም ዜጎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የዋልያ አይቤክስ ብሔራዊ ጥበቃ ስትራቴጂ ማዘጋጀት የውይይቱ አላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቢምረው ካሳ በበኩላቸው፤ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የበርካታ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ፓርኩን ህልውና ለመጠበቅ የሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ፣ የሚስተዋሉ ሰው ሰራሽ ችግሮችን በጠንካራ የጥበቃና ቁጥጥር ሥራዎች በጋራ መከላከል እንደሚገባ አንስተው፤ በቀጣይ የዋልያን ህልውና ለመጠበቅ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንዲሁም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግቱ ሥራዎች መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የዋሊያ ቀንድ እና ጥፍር ለባሕላዊ መድኃኒትነት ያገለግላል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት፤ የዋሊያ አይቤክስ እንስሳትን ማደን እየተበራከተ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ማሩ ቢያድግልኝ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት የዋሊያ አይቤክስ ብዛት ወደ 865 ደርሶ እንደነበር አንስተው፤ በሰሜኑ ጦርነት፣ በክልሉ የሰላም እጦት እና በሕገወጥ አደን መበራከት ምክንያት አሁን ላይ 306 ዋሊያዎች ብቻ መኖራቸውን ገልጸዋል።
አልፎ አልፎ የሚታየው የሰላም እጦት ለእንስሳቱ ጥበቃ ለማድረግ እንቅፋት መፍጠሩን ያነሱም ሲሆን፤ ጥብቅ ቁጥጥር ካልተደረገ ብርቅየ እንስሳቱ ላይ የመጥፋት አደጋ መጋረጡን ተናግረዋል።
ሕገ ወጥ አደን መበራከት፣ ልቅ ግጦሽ መኖር፣ በአካባቢው ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ መኖር ለዋሊያ ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።
በውይይቱም በዘርፉ ባለሙያዎች የተዘጋጁ የዋልያ አይቤክስ ስነ-ሕይወታዊ ባህሪ፣ የዋልያ አይቤክስን ጥበቃ ታሪካዊ ዳራ፣ አሁናዊ ሁኔታ፣ በዋልያ አይቤክስ ላይ የተጋረጡ ችግሮች፣ አገራዊ የዱር ሕይወትን ለመጠበቅ የወጡ ህጎችና ፖሊሲዎችን እንዲሁም ህልውናቸው ለአደጋ የተጋለጡ የዱር እንስሳትን ህልውና ለመታደግ በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላት ኬኒያ እየተገበረች ያለውን የዱር እንስሳት ጥበቃ ተሞክሮ ለተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡
የቀረቡትን ፅሁፎች መነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ የዋልያ አይቤክስ ብሔራዊ ጥበቃ ስትራቴጂ እቅድ የማዘጋጀት ሒደት በዛሬው ዕለት ቀጥሎ ይካሄዳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ