የካቲት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያስ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም የሚጀምረውን ዓብይ ጾም፤ "ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት ልናሳልፍ ይገባል" ሲሉ የቤተክርስቲያኒቷ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኩስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሐይማኖት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብጹዕነታቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት መልዕክት፤ "የዲያብሎስን የፈተና ወጥመዶች በጣጥሶ በድል አድራጊነት ለተገለጠው ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመ ኢየሱስ ሱባዔ እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ!" ብለዋል።

አክለውም የእምነቱ ተከታዮች ከኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀን እና ለሊት ጾም የሚወስዱት ብዙ ትምህርት መኖሩን በማንሳት፤ "ሕይወትን ማኖር የሚቻለው በእንጀራ ብቻ እንዳልሆነ ቃሉም ያስተምረናል" ሲሉ ገልጸዋል።
ስለሆነም ዳቢሎስን ድል ለማድረግ፤ በታላቁ የዓብይ ጾም ከመልካም ኅሊና የሚመነጭ መልካም ሥራ ማከናወን ማሳለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
"ጾምን የምንጾመው መልካም ኅሊና ኖሮን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ለመገዛት፣ ከዚያም ከቃሉ በተነገረን መሠረት የተራቡትን ልንመግብ፣ የተራቆቱትን ልናለብስ፣ የተጣሉትን ልናስታርቅ፣ ፍትሕ ያጡትን ፍትሕ እንዲያገኙ ልናደርግ፤ ለንኡሳን የሕብረተ ሰብ ክፍሎች የተለየ ትኵረት ልንሰጥ፣ እኩልና ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል በሰው ልጆች መካከል ልናረጋግጥ፣ ሰብኣዊ ክብር እንዳይነካ ጦርነት፣ ጥላቻ፣ አደገኛ የቃላት ውርወራና መነቃቀፍ እንዲቀር የግድ ነው" ብለዋል።

ስለሆነም "በሃላፊነት ያለን የበላይ የሕብረተሰቡ መሪዎች ፍትህ እና እኩልነትን በማስፈን፤ ከነገሮች ሁሉ በፊት ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት ጾሙን እንናሳልፍ" ሲሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ