የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ትናንት እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017ዓ.ም ለሊት 8 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ፤ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 3 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ከጭሮ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ሲሆን፤ ረዘም ላሉ ሰከንዶች የቆየው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተሰምቷል።

በተመሳሳይ በአዋሽ ከተማም ይኸው የመሬት መንቀጥቀጥ ቀላል የሆነ ንዝረት ማስከተሉን "ቮልካኖ ዲስከቨሪ" ባወጣው መረጃ አመላክቷል።

እንዲሁም በደብረ ብርሃን፣ ደብረ ሲና፣ ከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባቲና ደሴን ጨምሮ፤ በድሬዳዋ፣ ሂርና፣ ገለምሶ፣ ገዋኔ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ በዴሳ፣ ደደር፣ አቦምሳ፣ ገዋኔ፣ መተሐራና ወንጂ ከተሞች ላይ ተመሳሳይ አነስተኛ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት መከሰቱን ተቋሙ በመረጃው ጠቁሟል።

የመሬት መንቀጥቀጡ ከመሬት በታች 10 ኪ.ሜ ጥልቀት ላይ መከሰቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ንዝረቱም ከወትሮው የተለየ ጠንካራ እና እጅግ አስፈሪ እንደነበር አሐዱ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ነዋሪዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው መረጃ ለማወቅ ችሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ