የካቲት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የከተማዋ ነዋሪዎች የቤትና ቦታ ግብር ያለ ቅጣት እስከ የካቲት 30 እንዲከፍሉ ማሳሰቡን ተከትሎ፤ ነዋሪዎች የምንከፍለው ግብር ገቢያችንን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

በግብር አከፍፈል ወቅት ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ እና ከፍተኛ ወረፋ እንዳለ የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ "የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን መከተል ያስፍልጋል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም "የምንከፍለው ግብር ገቢያችንን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል" ያሉ ሲሆን፤ ያለው ብልሹ አሰራርም ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አሐዱ የነዋሪዎችን ጥያቄ መሠረት በማድረግ "የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን የአሰራር ሂደቱን ለማስተካከል እና ቅሬታውን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?" ሲል ጠይቋል።

Post image

የቢሮው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ የቀን ገቢ ግምት በከተማ ውስጥ የተጀመረው በ2009 ዓ.ም መሆኑን ገልጸው፤ በዛን ወቅት በተጠናው ጥናት መሠረት ግብር ከፋይዎች እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ ግብር ከፋዮች በሚኖሩበት ወቅት አሰራሩን ተከትሎ የቀን ገቢያቸው እንደሚተመን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በከተማዋ ያለው የግብር አከፋፈል ሂደት መሻሻሎችን ማሳየቱን ገልጸው፤ አብዛኛው ግብር ከፍይ በወቅቱ ግብሩን እየከፈለ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም በመዲናዋ ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን ግብራቸውን መክፈል ከሚጠበቅባቸው 429 ሺሕ 829 ባለይዞታዎች መካከል፤ እስካሁን 246 ሺሕ 725 ባለይዞታዎች ወይም 62 በመቶዎቹ ክፍያቸውን በወቅቱ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከጣሪያና ግድግዳ ግብር እስካሁን ከ3 ቢሊየን 60 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ከዚህ በፊት ውዝፍ ዕዳ ከነበረባቸው ባለይዞታዎች ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ወረፋ እና የመሳሰለው ነገር ተግዳሮት እንዳይንባቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቁት የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር፤ በወቅቱ ግዴታቸውን በማይወጡ ግብር ከፋዮች ላይ በየወሩ እየጨመረ የሚሄድ የአምስት በመቶ ቅጣት እንደሚጣል አሳስበዋል።

አክለውም "በቢሮዎች ላይ ብልሹ አሰራር አይኖርም ማለት አይቻልም" ያሉ ሲሆን፤ ይህን ለማስተካከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ