መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለአስጎብኚ ድርጅቶች በተለይም ሟሟላት ካለባቸው መኪና እና ቢሮ ጋር ተያይዞ የተቀመጠው መስፈርት፤ ሙያተኛውን ወደ ዘርፉ ከማስገባት አንፃር ችግር እንደሆነበት የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ዘርፉ አቅም ያለው ሰው ብቻ የሚገባበት እንደነበረ ለአሐዱ የገለጹት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሀብታሙ አስፋው ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ግን ለአስጎብኚ ድርጅቶች በፊት ይደረግ የነበሩ መኪናን ጨምሮ ሌሎች ማበረታቻዎች በመቅረታቸው ምክንያት ዘርፉን እየተቀላቀሉ የሚገኙ ድርጅቶች ጥቂቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም በየጊዜው በዘርፉ የሚመረቁ ተማሪዎች እየተቀላቀሉ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን በማንሳት፤ "በዚህም ምክንየት የግል አስጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል" ብለዋል።

Post image

ነገር ግን ሥራውን ለመስራት አስበው የሚመጡ እንዳሉ ሁሉ፤ ማበረታቻውን ብቻ ለመጠቀም የሚገቡ በመኖራቸው እንዲቀር ሲደረግ ተሳትፏቸው መቀነሱን ገልጸዋል።

አሐዱም በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበርን ያነጋገረ ሲሆን፤ በአንድ ጎኑ የቱሪዝም ሚኒስቴርን ሀሳብ የሚጋሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኤንዲ አሰፋ "ማበረታቻውን ለመጠቀም ብቻ ምንም አይነት የቱሪዝም ትምህርት ደረጃ የሌላቸው ሰዎች ዘርፉ ላይ ይሰማሩ ነበር" ብለዋል።

በሌላ በኩል አሁን ላይ የአስጎብኚ ድርጅቶች ሥራ ላይ ያለመሳተፍ ችግር ማበረታቻው በመቅረቱ ብቻ ሳይሆን፤ ለብቃት ማረጋገጫ የተቀመጠው መስፈርት በመሆኑ ብዙኃኑን የቱሪዝም ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ማድረጉን ተናግረዋል።

ማበረታቻ የሚያስፈልግ ቢሆንም በዘርፉ ግን የሚጠበቀውን ያክል ባለሙያ እንዳይኖር ያደረገው፤ የቱሪዝሙን ባለሙያ ወደ ዘርፉ አለማስገባትና የመመሪያ አስቸጋሪነት እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ሀብታሙ አስፋው በበኩላቸው፤ "በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት የነበረው መመሪያ ለአስጎብኚ ድርጅቶች ችግር እንደፈጠረ ታምኖበታል" ብለዋል።

በዚህም መሠረት በዘርፉ የተማሩና ልምድና እውቀት ያላቸው ሰዎች እንዲሳተፉበት ለማድረግ ሙያተኛውን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የመኪና መስፈርትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን ይቀርፉል የተባለለት መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ መመሪያው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ