መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ በኢተያ ከተማ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት የሃይል ማመንጨት ሂደት እንደሚጀምር ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ከንፋስ 100 ሜጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት በሂደት ላይ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል፡፡
የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ከውሃ፣ ከንፋስ እና ከጸሀይ የኤሌክትሪክ ኃይል እየመነጨ የሚገኝ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከውሃ ሀብት የሚመነጨው የኃይል አቅርቦት ነው፡፡
አክለውም ከንፋስ የሚገኘው የኃይል ማመንጨት ሂደት ከውሃ ቀጥሎ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም፤ በክረምት ወቅት ላይ ከንፋስ የሚገኘው የኃይል ማመንጨት አቅም የሚቀንስበት ሁኔታ ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
የንፋስ መጠን የሚጨምርበት እና የሚቀንስበት ተፈጥሯዊ ሁኔታ ስለመኖሩ የተናገሩት አቶ ሞገስ፤ ከዚህ በተጨማሪ በጥገና ምክንያት የኃይል ማመንጨት ሂደቱ ሊቋረጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በአሰላ በግንባታ ላይ የሚገኘው የንፋስ ኃይል ማመንጫ 100 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው የገለጹም ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ወደ ኃይል ማመንጨት ሂደት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከንፋስ 404 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም የተፈጠረ መሆኑ በማንሳት፤ በአራት ቦታዎች ማለትም በአዳማ ከተማ፣ በሶማሌ ክልል ሃይሻ እና በትግራይ ክልል አሸጎዳይ የኃይል ማመንጨት አገልግሎት ላይ እንደሚገኙ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፤ ከንፋስ 1 ነጥብ 3 ጊጋ ዋት ኃይል፣ ከውሃ ወደ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት እንዲሁም ከእንፋሎት ደግሞ ወደ 10 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል እየመነጨ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው አክውም ከንፋስ በተጨማሪም ከእንፋሎት የሚገኘው የኃይል ማመንጨት በሁለት መንገድ እንደሚከናወን የተናገሩ ሲሆን፤ "አንደኛው ደረቅ ቆሻሻን በማቃጠል በሚፈጠረው ሙቀት እንፋሎት ወደ ኃይል የመቀየር እና የከርሰ ምድር እንፋሎት ናቸው" ብለዋል፡፡
ከከርሰ ምድር የሚገኘው እንፋሎት በዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 7 ነጥብ 4 ሜጋ ዋት ሃይል በማመንጨት በሁለት ዙር 70 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እንደሆነ እና የአንደኛ ዙር ቁፋሮ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም በትምርት ተቋማት ላይ ዘርፉን በተመለከተ እራሱን የቻል ስልጠና እንደሚከናወን የገለጹ ሲሆን፤ በኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን ካከናወኑ በኋላ የአቅም ማሳገደጊያ እንደሚወስዱም ተናግዋል፡፡
ተቋሙ የሥራ ሂደቱን ባሉት የዘርፉ ባለሙያዎች እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ የባለሙያ እጥረት ስለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም "ያሉትን ባለሙያዎች ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል፡፡
100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከዴንማርክ መንግሥት በተገኘ ብድር እና ዕርዳታ ከ146 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በጀት ታሕሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ እያንዳንዳቸው 3 ነጥብ 46 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያላቸው 29 የንፋስ ተርባይኖች አሉት፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ የኃይል ማመንጨት ሂደት በተያዘው ዓመት እንደሚጀምር ተገለጸ
