መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች መሠረታዊ የምርት ፍጆታዎች እና የትራንስፓርት ክፍያ ዋጋ መናሩን አሐዱ ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በክልሉ ባለው የነዳጅ እጥረት ምክንያት የትራንስፖርት ታሪፍ ክፍያ በእጥፍ ጨምሯል ያሉት የክልሉ ነዋሪ፤ በ50 ኪ.ሜ መንገድ ቀድሞ ከነበረው 150 ብር ወደ 300 ብር መጨመሩን ገልጸዋል።
የትራንስፖርት ክፍያው ከእጥፍ በላይ የጨመረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም መኖራቸውን ጠቁመዋል።
"ይህን የትራስፖርት ክፍያ ከፍለው መጓዝ የማይችሉ ነዋሪዎች አሉ" ያሉም ሲሆን፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ ለመንቀሳቀስ ነገሮችን አዳጋች ማድረጉንም ተናግረዋል።
ሌላው አሐዱ ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪ፤ "አላቂ የሆኑ እንደ በርበሬ፣ ዘይት እና ጤፍ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ አሳይተዋል" ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም አንድ ሊትር ነዳጅ ከ260 ብር እስከ 300 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የኑሮ ውድነት የሚታወቅ ነው" ያሉት ነዋሪዎቹ፤ "በክልሉ ህወኃት የገባበት ሰጣ ገባ ምርቶች እንደልብ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል" ብለዋል።
እንዲሁም በመጋዘን ውስጥ ምርት የሚደብቁ ነጋዴዎች መኖራቸው የጠቆሙ ሲሆን፤ ያም ቢሆን ሕብረተሰቡ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል በስፋት እየሸመተ መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም የነዳጅ ምርት በሕገ-ወጥ መንገድ እየተሸጠ መሆኑና ይህም በትራንስፓርት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲኖር ማድረጉን አንስተዋል።
"በአጠቃላይ በክልሉ ያለው የጸጥታ ስጋት ለነጋዴው ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል" ሲሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በትግራይ ክልል የመሠረታዊ ምርት እና የትራንስፖርት ክፍያ ዋጋ መናሩ ተገለጸ
