መጋቢት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ከጣሪያና ግድግዳ ግብር 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የጣሪያና ግድግዳ ግብር እንዲከፍሉ የውሳኔ ሀሳብ ማስተላለፉ ይታወቃል።
የጣሪያና ግድግዳ ግብር መክፈያ ጊዜ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲከፈል የተቀመጠው ቀነ ገደብ ካላፈ፤ በቅጣት እና ወለድ ክፍያ እንደሚስተናገዱ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ መግለጹ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰውነት አየለ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ 475 ሺህ ዜጎች የጣሪያና ግድግዳ ግብር መክፈል አለባቸው በሚል ተለይተዋል።
"ከዚህም 433 ሺሕ የሚሆኑት ማለትም 91 በመቶ የሚጠበቅባቸውን ግብር ከፍለዋል" ያሉ ሲሆን፤ በዚህም 7 ነጥብ 2 ቢሊየን የሚሆን ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የተቀሩት 42 ሺሕ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በቅጣት የግብር ክፍያው እየተፈጸመ መሆኑንም በመግለጽ፤ ቀን በጨመረ ቁጥር የወለድ ክፍያው እየጨመረ እንደሚሄድ አሳስበዋል።
"ቀኑ በጨመረ ቁጥር የሚከፈለው የወለድ መጠን ይጨምራል" ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ሰውነት፤ ከ2013 ጀምሮ የሚከፍሉ መኖራቸውን ጠቁመው ከመደበኛው በእጥፍ የሚከፈልበት ሁኔታ መኖሩን አብራርተዋል።
የጣሪያና ግድግዳ ግብርን በተመለከተ በበርካቶች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የጣሪያንና ግድግዳ ግብር አከፋፈል ቀድሞ የነበረ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "የጣሪያና ግድግዳ ግብር አትሰብስቡ ብሎ የከለከለን የለም" ሲሉም ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም።
የክፍያ መጠኑ ሕጉ ሲወጣ የነበረው የቤት ኪራይ ዋጋ በነበረው አሁን ደግሞ አሁን በሚከራይበት ዋጋ የሚሰላ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ከጣሪያና ግድግዳ ግብር 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ
