መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከወላጅ እናቷ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የ2 ዓመት ሕጻን ልጁን ጉሮሮዋን አንቆ በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለ በኋላ አስከሬኗን መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የጨመረው ግለሰብ በእስራት መቀጣቱን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በደሎቻ ከተማ አስተዳደር ፈረጃት 02 ቀበሌ ልዩ ሥሙ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ እንደሆነ ፖሊስ መምሪያው ለአሐዱ በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ የሕጻኗ እናት ከሆነችው ባለቤቱ ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የስጋ ልጁን አንገቷን አንቆ ህይወቷን ካሳለፈ በኋላ 10 ሜትር ጥልቀት ባለው የመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ማስገባቱ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡
ጥቆማ የደረሰው የደሎቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎ የሕጻኗን አስከሬን ከመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ከሁለት ቀን በኃላ በማውጣት አስከሬኑን ለምርመራ ወደ ወራቤ ኮምፕሬሲብ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መላኩ ተገልጿል።
ፖሊስ የምርመራ ውጤቱን በመያዝ ለተፈጸመው ድርጊት አስፈላጊ የሆኑ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አሰባስቦ፣ ምርመራውን በማጣራት መዝገብ አደራጅቶ ለስልጤ ዞን ዓቃቤ ሕግ አቅርቧል።
በዚህም ዓቃቢ ሕግ ከፖሊስ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ አይቶና ፈትሾ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኤ.ፌ.ድ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1)(ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በፈጸመው ከበድ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ መስርቶ ለስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ማቅረቡንም አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱም ከዓቃቤ ሕግ የቀረበለትን የነፍስ ግድያ ወንጀል ክስ የቀረበለትን ተገቢ የሆነ ማስረጃ መሠረት በማድረግ የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ተከሳሽን ያርማል፤ ሌሎችን መሳል ድርጊት የሚፈጽሙ አካለትን ያስተምራል በማለት፤ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ተከሳሽ ደጀኔ መኮንን ገ/ፃዲቅ በዕድሜ ልክ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የ2 ዓመት ሕጻን ልጁን ገድሎ አስከሬኗን መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የጨመረው አባት በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጣ
