መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመዲናዋ በሚስተዋለው የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ምክንያት፤ ከ280 በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች ከሚሰሩበት የመንግሥትና የግል መስሪያ ቤቶች ሥራቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር አስታውቋል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገለታው ሙሉ ለአሐዱ እንደገለጹት በከተማዋ የሚሰጡ የትራንስፖርት አገልግሎቶች የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት በሚፈለገው ልክ ያማከሉ ባለመሆናቸው፤ በርካቶች የሚወዱትን ሥራ አቋርጠው ቤት ውስጥ ከተቀመጡ ረጅም ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

በከተማዋ ለአካል ጉዳተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት በሚፈለገው ልክ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በሥራ ሰዓት በሚያረፍዱ የአካል ጉዳተኞችም ከሌላው ሠራተኛ እኩል ደመወዝ እንደሚቀረጥባቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተለያየዩ የመንግሥትና የግል መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው የሚሰሩ የአካል ጉዳቶች የተለያዩ የሰብዕዊ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸውም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በከተማዋ ለልማት ተብለው የተቆፈሩ ጉድጓዶች ክፍት በመሆናቸው ምክንያት፤ 16 የአካል ጉዳተኞች ገብተው ለተጨማሪ አደጋ መጋለጣቸውን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገለታው ሙሉ ገልጸዋል፡፡

ከመንገድ ግንባታ ጋር የተገናኙ ተቋማት የሚሰሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉደተኞችን ያማከለ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

አክለውም በከተማዋ የሚሰሩ የመሠረተ ልማቶችን የሚደገፉ ቢሆንም የአካል ጉዳተኞችን ከሥራቸው የሚያፈናቅል እንዲሁም ለጉዳት ተጋላጭ በማያደርግ መልኩ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህም ምክንያቶች "የአካል ጉዳተኞችን የእንቅስቀሴ የተገደበ መሆኑ ለከፍተኛ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓል" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

"መንግሥት የአካል ጉዳተኞች ዜጋ መሆናቸውን ከግምት ዉስጥ ማስገባት አለበት" ሲሉ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቱ፤ "ማንኛውም እድገት አካታችነትን በሚገባው ልክ እውን ሲደረግ ነው ትክክለኛ እድገት የሚባለው" ብለዋል።

"ነገር ግን አሁን እየታደ ያለው ይህ አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ "መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ለአካል ጉዳተኞች ጥያቄ እልባት ሊሰጥ ይገባል" ሲሉም ጠይቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ