የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የፊታችን የካቲት 8 እና 9 በመዲናዋ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ሲሆን፤ በጉባኤው ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ከበፊቱ የበለጠ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው በማድረግ የተሻለና ከፍተኛ የሆነ ገቢን ለመሰብሰብ መታቀዱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
አንዲት ሀገር ጤናማ የሆነ የቱሪስትን ገንዘብ አስቀረች የሚባለው ኬላ ጥሎ ክፍያ በማስከፈል ብቻ ሳይሆን፤ ዘርፈ ብዙ የአገልግሎት መስኮችን ስታሰፋ መሆኑን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መሪ ስራ አስፈፃሚ ጌትነት ይግዛው ለአሐዱ ገልጸዋል።
በመሆኑም ዋናው ጤናማ የሆነ የቱሪስትን ገንዘብ ወደ ሀገሪቱ እንዲቀር ማድረጊያ መንገድ የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም ስለሆነ፤ ለዚያም ሲባል ከተሞችን እንደገና የማልማት ሥራን ጨምሮ አንዳንድ የሰላም እጦት ካለባቸው ቦታዎች በስተቀር ከአዲስ አበባ ውጪ ክልሎችን እንዲጎበኙ የማድረግ ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
"ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ከ1 ሺሕ 500 እስከ 2 ሺሕ እና ከዚያ በላይ ተሳታፊዎችን የሚገኙበት ስለሆነ፤ የቱሪዝሙን ዘርፍ ከማነቃቃት በዘለለ የሀገሪቷን የቱሪስት ፍሰት ቁጥር በእጅጉ የሚቀይር በመሆኑ ከተለመደው ሁለትና ሦስት ቀን ውጪ አምስትና ስድስት ቀናትን እንዲቆዩ የማድረግ ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

ከአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በተጨማሪ በዚህ ወር ብቻ የመጀመሪያ የሆነው "አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር" ምርቃትና የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር የዓለም አቀፍ ጉባዔ እንደሚካሄዱ ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስፈፃሚው ሀገሪቱ በዚህ በጀት ዓመት ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን፣ ኮንፈረንሶችንና ኤቨንቶችን ስለምታካሂድ ከባለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ የቱሪስት ፍሰትና የተሻለ ገንዘብ ይገኛል ተብሎ እንደሚታሰብም ጨምረው ተናግረዋል።
በነገው ዕለት በሚጀመረውና ለአምሥት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት ባለስልጣናት አዲስ አበባ መግባት የጀመሩ ሲሆን፤ እስከ አሁን የአልጄሪያ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ሞሪታኒያ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ካሜሮን፣ ቦትስዋና፣ ሌሴቶ፣ ናሚቢያ፣ ሴኔጋል እና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ