የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሽረ እንዳስላሴ ከተማ ቀበሌ 05 በሚገኝ በመዝናኛ ስፍራ ላይ ትናንት የካቲት 3 ቀን 2017 ከምሽቱ 1 ሰዓት 30 የተወረወረ የእጅ ቦንብ ፈንድቶ፤ በአጠቃላይ 17 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሽረ እንዳስላሴ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አወጣኸኝ መሰለ፤ ከሰሞኑ የመዝናኛ ማዕከሉ ባለቤት አቶ ባራኪ ሀጎስ ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች በስልክ ጥሪ እና በፅሁፍ መልዕክት 'ገንዘብ እንዲልኩ ካልሆነ አደጋ እንደሚደርስባበው' ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ትናንት ማምሻውን አደጋው መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ "በአደጋው አምስት ሠራተኞች እና 12 የመዝናኛ ማዕከሉ ተጠቃሚዎች በአጠቃላይ 17 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።

የከተማው ፖሊስ ከጸጥታ አካላትና ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ከምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖች የተውጣጡ የፖሊስ አባላትን ያካተተ ኮሚቴ በማዋቀር፤ አስፈላጊውን የጸጥታና ክትትል ለማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን ኢንስፔክተር አወጣኸኝ አስታውቀዋል።
በወንጀሉ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ