የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የታጠፈ የደበዘዘ የተፋፋቀ እና በአጠቃላይ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው እየተባባሰ ለመጣው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ልዩ ልዩ የደምብ መተላለፍ ጥፋቶች እንደ ምክንያትነት የሚገለጹ ቢሆንም፤ ለእይታ ግልፅ ያልሆኑ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች መበራከት ለአደጋ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ የደምብ መተላለፍ ጥፋቶች ከአንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሦስት ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች በትራፊክ ፖሊስ አባላት ብቻ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በጥር ወር 2017 ዓ.ም ብቻ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ከ2 ሺሕ 100 በላይ አሽከርካሪዎች እርምጃ መወሰዱን ተመላክቷል፡፡
በየጊዜው የታጠፈ የደበዘዘ እና የተፋፋቀ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ደረጃ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ፖሊስ ገልጿል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓትን በመፍጠር ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ታምኖበታል ተብሏል።
በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው ደምብ ቁጥር 557/2016 መሰረት ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ ጥፋቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ 1 ሺሕ 500 ብር የሚያስቀጣ ደምብ መተላለፍ መሆኑን ተደንግጓል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የአደጋም ሆነ የወንጀል ስጋቶችን መቀነስ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ፤ በመደበኛነት ከሚያከናውነው የትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ጎን ለጎን ከየካቲት16 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በዘርፉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የታጠፈ፣ የተቆረጠ፣ የደበዘዘ እና በአጠቃላይ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩን በማረም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ
በጥር ወር ብቻ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ከ2 ሺሕ 100 በላይ አሽከርካሪዎች እርምጃ ተወስዷል
