መጋቢት 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፋት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ረዳ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት በመሆን በይፋ ተሹመዋል፡፡

Post image

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ባለፈው አንድ ወር ገደማ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት፣ የፕሪቶርያን ስምምነት እና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ምክር በማከል ሰፊ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

Post image

"የአቶ ጌታቸው የሥልጣን ዘመን በሕጉ መሠረት ሲያበቃ የሚቀሩ ቁልፍ ሥራዎችን የሚያከናውን አካል፣ ግዝያዊ መንግሥቱ መቀጠለ አለበት የሚል ድምዳሜ ከተያዘ በኋላ፣ ይሄንን ሽግግር ማን መርቶ ከግብ ሊያደርስ ይችላል? የሚሉ ውይይቶችን ስናደርግ ቆይተናል" ብለዋል፡፡

አክለውም በዛሬው ዕለት በይፋ እና በሰላማዊ መንገድ በአዲስ ባህል የሥልጣን ሽግግሩን እና ቅብብሎሹን ለማካሄድ የተዘጋጀ ፕሮግራም መከናወኑን ተናግረዋል።

Post image

"ጄኔራል ታደሰ ባለፋት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ምክትል ሆነው ያገለገሉ ሰው ናችው፡፡ ባለፋት ሁለት ዓመታት የነበሩ ድካሞችን እና ጥንካሬዎችን በግልጽ የሚገነዘቡ ሰው ናቸው። አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት በብዙ አካላት የታመነ ነው።" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

Post image

በመጨረሻም "የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላም እና ልማት፣ እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት ስናሳካ፣ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ።" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ