ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የገቢዎች ሚኒስቴር ልዩ መለያ ኮድ (QR Cod) የተካተተበት የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ የማቅረቢያ ቀነ ገደብ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ የደረሰኝ ህትመት አሰራር ሂደትን አስመልክቶ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር የገቢ ዘርፍ አመራሮች ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይም ከዚህ ቀደም የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ ማቅረብ የሚቻለው እስከ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ብቻ መሆኑ በተገለጸው መሰረት፤ ቁጥራቸው 88 ሺሕ 717 የሆኑ ግብር ከፋዮች የህትመት ጥያቄ ማቅረብ መቻላቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የህትመት ጥያቄያቸውን ያላቀረቡ ግብር ከፋዮች መኖራቸውና ይህን ታሳቢ በማድረግ የህትመት ጥያቄ ማቅረቢያ ቀነ ገደብ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም በውይይቱ መወሰኑ ተነግሯል፡፡

Post image

እንደ ሀገር በገቢው ዘርፍ የሚሰተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ "በተለይም የማንዋል ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር ስርዓትን በማሻሻል የሚፈለገውን የገቢ ዕድገት ማስመዝገብ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

ልዩ መለያ ኮድ (QR Cod) የተካተተበት ሚስጥራዊ የደረሰኝ ህትመት ሥርዓትን ወደሥራ ማሰገባት የሚያስፈልግ መሆኑን ያስገነዘቡም ሲሆን፤ እስከ አሁን ባለው አፈፃፀም ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የክልል እና ከተማ አስተዳደር የገቢ ዘርፍ አመራሮች በበኩላቸው፤ "ሕገ-ወጥነትን እና የታክስ ማጨበርበር ወንጀሎችን ከመከላክል አንፃር የደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር ሥርዓታንን በልዩ መለያ ኮድ (QR Cod) የተደገፈ እንዲሆን ማደረጉ ተገቢና ተክክለኛ ውሳኔ ነው" ብለዋል፡፡

Post image

እስከ አሁን በነበርው የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ እና ስርጭት ሂደት በተሰተዋሉ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በተለይም አንዳንድ ግብር ከፋዮች በተቀጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በተሟላ መለኩ የህትመት ጥያቄያቸውን ያለማቅረብ፣ የሲሰተም መቆራረጥ፣ በተፈጠረው መጨናነቅ ምክንያት የህትመትና ስርጭት መዘግየት እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ ክፍተቶች መታየታቸው ተጠቅሷል፡፡

የታዩ ክፍተቶችን ለማረም እንዲቻል በተለይም እስከ አሁን ድርስ የህትምት ጥያቄ ያላቀረቡ ግብር ከፋዮች በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የህትምት ጥያቄ እንዲያቀርቡ እድል መሰጠቱም ነው የተመላከተው፡፡

በዚህም መሰረት የሲስተም መጨናነቅ እንዳይፈጠር የሲስተም ማሻሻያዎችን ማከናውን፣ የህትመት እና ስርጭት ተግባራት በሚፈለገው ደረጃ ለማከናወን ተጨማሪ የህትመት ማሽኖችን ወደ ሥራ ማስገባት እና አትሞ በፍጥነት ማሰራጨት እንደሚገባ ከስምምነት ላይ መደረሱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ