ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በትላትናው ዕለት በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል፡፡

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ወደ አሜሪካ ማቅናታቸውን ተከትሎ፤ የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን በምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ አካሂዷል፡፡

Post image

በጉባኤውም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነጎ፤ የቤተሰብ ምዝገባ የመንግሥት አገልግሎቶችን እና የዜጎችን ወሳኝ ኩነት መረጃ በተደራጀ መልኩ ለመያዝ እንደሚረዳ ባቀረቡት ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ ላይ ገልጸዋል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት በኃላ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎቻቸውን ያነሱ ሲሆን፤ በተለይም በጎዳና ተዳዳሪ ልጆች፣ በፍቺ እና ጋብቻ ዙሪያ እንዲሁም ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽም በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነጎ እና በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በኩል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

Post image


የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ከምክር ቤት አባላት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ በሰጡት ምላሽ፤ "አዋጁ በሀገሪቱ በየትኛውም አቅጣጫ ያለን ሕዝብ መዝግቦና ሰንዶ ለመያዝ የሚረዳ አዋጅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ከኢሚግሬሽን ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ችግር የነበረው ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ ነበር" ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከደህንነት ጋርም አደጋ ሲያስከትልብን የነበረ በመሆኑ የዘመነ ምዝገባ በማስፈለጉ ይህ አዋጅ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም ብለዋል፡፡

ሌላኛው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነጎ በበኩላቸው፤ ከጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች ጋር በተያያዘ 'ሌሎች አካላት ይከታተሉታል' የተባለውን የሴቶችና ሕጻናት፣ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲከታተለው የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Post image

ከዚህ በተጨማሪ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን የገለጹት ምክትል አፈ ጉባኤው፤ ረቂቁ ከሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር የነበረ ሲሆን 'ይመለከተዋል' ተብሎ በዚህ ቋሚ ኮሚቴ የታየ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም "ከምክር ቤቱ እንደተነሳው አዋጁ ላለተፈለገ ዓለማ እዳይውል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዋጁም በምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት ከተካሄደበት በሗላ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ