የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም ያካተተ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ከተፈለገ፤ መንግሥት ሰላም የማስፈን ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳስቧል።
በተመሳሳይ ሁሉም ታጣቂ ሃይሎች ወደ ምክክር እንዲመጡ ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም፤ "በመርህ ደረጃ እንኳን ይህንን ተቀብሎ የመጣ ታጣቂ ሃይል የለም" ሲሉ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ተናግረዋል።
"ጦርነት ጦርነትን አያቆምም" ያሉት ኮሚሽነሩ መንግሥትም ሆነ "ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል" ብለዋል።
ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ከታጣቂ ሃይሎች ጋር ንግግር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውና ከታጣቂዎች ጋር ተገናኝቶ ለመነጋገር ኮሚሽኑ የደህንነት ጥበቃ እንደሚያደርግ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ መግለጻቸው አይዘነጋም።
በትላትናው ዕለት ኮሚሽኑ የሦስት ዓመት የሥራ ግዜውን በተመለከተ ማብራሪያ ለመገናኛ ብዙሃን አካላት የሰጠ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ "የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፋፋይ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ኮሚሽነሩ ይህንን ያሉት 'በቅርቡ ከአንድ የታጠቂ ሀይል አመራር ጋር ግንኙነት አድርጋችኋል' በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።
ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አንድ የታጣቂ አመራር ወደ ምክክር መምጣት ማሰቡን እንደገለጸላቸውና እንዳነጋገሩት ተናግረዋል።
በዚህም ኮሚሽነሩ ከደህንነት አካላት ጋር በመነጋገር እነዚህን ታጣቂ ሃይሎቾ ወደ ምክክር ለማምጣት ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም ዋና ኮሚሽነሩ ከየትኛው የአማራ ክልል ታጣቂ አመራር ጋር ተገናኝተው እንደተወያዩ አልገለጹም።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከታጣቂዎች ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል በተካሄደዉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወጥቶ ከመንግሥት ጋር ድርድር ካደረገዉ የጃል ሰኚ ቡድን ጋር መምከሩ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
መንግሥት ሰላም ለማምጣት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳሰበ
በአማራ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አንድ የታጣቂ ብድን አመራር ወደ ምክክር መምጣት ማሰቡ ተነግሯል
