የካቲት 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የተገነባው እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው፤ የሕጻናት የነርቭ እና ህብለሰረሰር ቀዶ ጥገና ሕክምና የልህቀት ማዕከል በዛሬው ዕለት ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የልህቀት ማዕከሉን መርቀው ሥራ ያስጀመሩ ሲሆን፤ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች የተሟሉለት ማዕከሉ በዓመት ከአምስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የልህቀት ማዕከሉን "ለሀገራችን ሕጻናት ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው እንዲሁም ከተማችንን ሕጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ ለማድረግ የጀመርነውን ሥራ የሚደግፍ ነው" ብለዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተገልጋዮች ፍላጎት ለማስተናገድና በጤናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ተሰጥሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ከንቲባዋ፣ "በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ለገነባነው ለዚህ የልህቀት ማዕከል የሪች አናዘር ፋውንዴሽን ላደረገልን አስተዋፅዖ በነዋሪዎቻችን እና በራሴ ሥም ላመሰግን እወዳለሁ" ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ