የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ሕብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የአህጉሪቱ መንግሥታት ለቀጣናዊ ውህደት፣ ለእርስ በርስ ንግድ እና ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ፈተና የሆነውን የቪዛ ገደብ እንዲያስቀሩ እየተጠየቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የቪዛ ገደብ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የእርስ በርስ ንግድ እድገት እንዳያሳይ ዋና እንቅፋት መሆኑን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንን ለመፍታት የአፍሪካ መሪዎች በአፋጣኝ እንዲተገብሩት ይጠበቃል፡፡

ከቪዛ ነፃ እንቅስቃሴን በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተግበራዊ መደረጉ ለኢትዮጵያን የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በተመለከተ አሐዱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር አቡሌ መሐሪ ይህ ነፃ የቪዛ እንቅሰቃሴ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናው ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተው፤ "ዋነኛ ግቡም የሰው ሃይል እና አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህም በሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከሩ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያሳድግ በመሆኑ፤ ይሄ ለሀገራት የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

"ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ጋር ተያያዥ ስለሆነ ሰዎች እንዲሁም ሀገራት ገበያ ከመፍጠር አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል" ሲሉም አክለዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የ2025 የነፃ ቪዛ ዘመቻ ማስጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ዘመቻ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የንግድ ተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰቦች በአህጉሪቱ ካለ ቪዛ እንቅስቃሴ ዕቅድ ትግበራ እንዲፋጠን ጥረት ያደርጉበታል ተብሏል።

ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኒዮስ በርህተስፋ "አፍሪካውያን አንድ በመሆን ኢንቨስትመንትን ሊያሳድጉ ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"ከቪዛ ነፃ እንቅስቃሴው በተለይም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፓ እና ሌሎች ሀገራት ከመጓዝ በአፍሪካ ሀገራት በመሄድ ሥራዎችን መስራት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል" ብለዋል፡፡

ጋና፣ ሩዋንዳ፣ ጋምቢያና ቤኒን አፍሪካውያን ያለምንም ቪዛ አገራቸውን መጎብኘት እንደሚችሉ ካስታወቁ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ይገኙበታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ