የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለ1446 ዓ.ሒ የሐጅ ጉዞ ማመልከት የሚፈልጉ ሙስሊም የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት፤ ባሉበት ቦታ ሆነው ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባዘጋጀው ድረ ገጽ ላይ መረጃቸውን እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርቧል።

ምክር ቤቱ የዘንድሮውን ሐጅ ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል፡፡

መደበኛ የሁጃጆች ምዝገባም ከጥር 15/2017 ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተዘጋጁ የምዝገባ ጣቢያዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

"የዲያስፖራው ሙስሊም ማህበረሰብ የሐጅ አገልግሎት ለማግኘት ያለውን ጥያቄ እና ፍላጎት መነሻ በማድረግ፤ መጅሊሱ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጅት ያለው ቢሆንም፤ በሳዑዲ አረቢያ ሃጅ ሚኒስትር መመሪያ መሰረት አምናም ሆነ ዘንድሮ ምዝገባ ማካሄድ አልቻለም" ሲልም ገልጿል።

Post image

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ምክር ቤቱ አገልግሎቱ እንዲፈቀድ ጥረቱን በመቀጠሉ የሳዑዲ አረቢያ ሐጅ ሚንስቴር ሕጅ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸውን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን ሥም ዝርዝርና በኢትዮጵያ በኩል ሐጅ ለማድረግ የፈለጉበትን ምክንያታቸውን እንዲልክ ምክር ቤቱን መጠየቁን አስታውቋል።

በመሆኑም ለሐጅ ጉዞ ማመልከት የሚፈልጉ ሙስሊም የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ባሉበት ቦታ ሆነው ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባዘጋጀው ዌብሳይት ( https://hajj.et/diaspora/register ) አማካይነት መረጃቸውን እንዲልኩ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም በፌዴራል መጅሊስ በሚገኘው ልዩ የምዝገባ ጣቢያ ፓስፖርታቸውንና ምክንያታቸውን ይዘው በአካል በመቅረብ፣ አሊያም ሲስተሙ የሚጠይቃቸውን መረጃዎች በ +251 911873529 ስልክ ቁጥር በቀጥታ በመደወል እና በዋትስአፕ ወይንም በኢሜይል አድራሻ ethiohajj@gmail.com መረጃቸውን እንዲልኩ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ አክሎም ከሳውዲ ሀጅ ሚንስተር በኩል መልስ እስከሚሰጥ ድረስ በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጠይቋል፡፡

ስለቀጣይ ሂደቶች መጅሊሱ ተጨማሪ ማብራሪያ እስከሚሰጥ ድረስ ምንም አይነት ክፍያ እንዳይፈጽሙ የጠየቀው ጠቅላይ ምክር ቤቱ፤ ከዛሬ የካቲት 3/2017 እስከ የካቲት 9/2017 ድረስ ብቻ ከላይ በተቀመጡት መንገዶች አማካኝነት መረጃቸውን ማጋራት የሚችሉ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከተጠቀሰዉ ቀነ-ገደብ ውጪ የሚደርሱ/የሚቀርቡ መረጃዎች ተቀባይነት እንደሌላቸውም ጠቅላይ ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ