የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል በተያዘው ግማሽ ዓመት ብቻ በሕገ-ወጥ ንግድ ተሰማርተው በነበሩ ከ468 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

የቢሮዉ የኢንስፔክሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቆጲሳ፤ "በክልሉ በሕገ-ወጥ ንግድ ተስማርተው በሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ በመሰረታዊ ሸቀጦች ከ92 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ ናቸው" ብለዋል፡፡

በተያዘው ግማሽ ዓመት ከ11 ሺሕ 700 በላይ የንግድ ድርጊቶችን ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ ከ92 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ ያለ ንግድ ፈቃድ መስራት፣ ንግድ ፈቃድ ሳያድሱ መነገድ፣ ዋጋ ሳይለጥፉ መሸጥ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች በገበያ በማቅረብ እንዲሁም ዋጋ ጨምሮ በመሸጥ ሲሰሩ የተገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃው መወሰዱን አስረድተዋል፡፡

የእርምጃ አወሳሰዱን በተመለከተም አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አንስተው፤ ከጹሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በሕግ እስከ መጠየቅ የሚደርሱ እርምጃዎች የተወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ክትትል በማድረግ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቀረት በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኝ አንስተው፤ በዚህም ከ376 ሺሕ ሊትር በላይ የሚሆን ነዳጅ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ "ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይቱን ባከናወኑ አካላት ላይም ተገቢው እርምጃም ተወስዷል"ም ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ከሚመለከተው አካል በጋራ በመሆን እየሰሩ እንደሚገኝ እና ለማህበረሰቡ በተመጣጣን ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት እየሰሩ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ