የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከኦክስጅን መድኃኒት ምርት ይልቅ፣ የምርቱ ማስቀመጫ ዕጥረት እና የጤና ተቋማት የአጠቃቀም ችግር የአቅርቦት ዕጥረት እንዲኖር ማድረጉን ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የሕክምና አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ የሆስፒታል ዲያጎንስቲክ ዴስክ አስተባባሪ አብይ ዳዊት እንደገለጹት፤ የሆስፒታሎች የአጠቃቀም ችግርና በቂ ማስቀመጫ አለመኖር እክል በመሆኑ በሕክምና አሰጣጡ ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
"ዋናው ምርቱ ብቻ ሳይሆን ምርቱን ወደ ተጠቃሚው እንዴት ማድረስ መቻል ነው" የሚሉት ዴስክ ኃላፊው፤ ወደ እያንዳንዱ ተጠቃሚ ለማድረስ የኦክስጂን ሲሊንደር ዋነኛው አስፈላጊ ግብአት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቂ አቅርቦት ለተቋማቱ ማቅረብ ቢቻልም የአጠቃቀም ችግር ምክንያት፤ መድኃኒቱ ለተገልጋዮች እንዳይደርስ አድርጓል ሲሉም አክለዋል።
ከዚህ ቀደም አንድ ብቻ ምርቱን ማምረት የሚችል ተቋም መኖሩንና አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኦክስጂን ማምርት የሚችሉ ከ40 በላይ ተቋማት መኖራቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ነገር ግን የአምራቾችን የማስቀመጫ ግብአት ችግር ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
ዴስክ አስተባባሪው አያይዘውም የቀድሞዎቹ ሲሊንደሮች ሌሎች ሕሙማኑን እየረዱ በመሆኑ፤ በሀገር ውስጥ አዲስ የማምረት ሥራ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
"የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሌላቸው አካባቢዎች በሲሊንደር እንዲጠቀሙ ይደረጋል፤ ጥሩ የኤሌትሪክ አቅርቦት ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ በመጠኑ ቀላል የሆነና ከአንድ ስፋራ ወደሌላ ስፍራ ማንቀሳቀስ የሚቻል ኦክሲጂን ኮንሰንትሬተር በኤሌትሪክ ኦክስጂን እያመረተ ለታካሚው የሚሰጥ አለ" ብለውናል።
አያይዘውም የአቅርቦት ፈላጊውን በመረዳት ምርቱን በስፋት ማምረት ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተደጋጋሚ ጊዜ በጤና ተቋማት የኦክስጅን መድኃኒት አቅርቦት ሳቢያ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ አቤቱታዎችን ሲያሰሙ ይደመጣል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከኦክስጅን ምርት ይልቅ የኦክስጅን ማስቀመጫ እቃ እጥረት እክል እንደሆነበት ጤና ሚኒስቴር ገለጸ
