የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከ200 በላይ የአሳ ዝርያዎች ቢኖሩም፤ ጥቅም ላይ የሚውሉት 40 የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአሳ ሀብት ዴስክ ኃላፊ ፋሲል ዳዊት (ዶ/ር)፤ ካሉት የአሳ ዝርያዎች ውስጥ 40 ያህሉ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የአሳ ዝርያዎች ስለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም ከ200 የአሳ ዝርያዎች ወስጥ በገበያ ላይ ከሚገኙት 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን አንስተው፤ "ለዚህም ምክንያቱ በህብረተሰብ ዘንድ የአሳ ምርቶችን ለመጠቀም ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው" ብለዋል፡፡

የአሳን ምርት ከማምረት በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለውጭ ሀገር ገበያ እስኪቀርብ ድረስ ያለው ሂደት ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ በሀገር ውስጥ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምዝገባ በማድረግ እውቅና አግኝተው የአሳ ምርትን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ባለሃብቶች ቁጥር ከስድስት እንደማይበልጥም ተናግረዋል፡፡

Post image

የአሳ ምርት ለአረብ ሀገራት የውጭ ገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ የገለጹም ሲሆን፤ ለጎረቤት ሀገራት ከሚላባቸው መካከል ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እንዲሁም ጅቡቲ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በአረብ ሀገራት ያለውን የአሳ ምርት ገበያውን ለማሳደግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየሰሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ለውጭ ገበያ የአሳ ምርት የሚያቀርቡ ማህበራትን ቁጥር በቀጣይ ለመጨመር በእቅድ ስለመያዙም በግብርና ሚኒስቴር የአሳ ሀብት ዴስክ ኃላፊው ፋሲል ዳዊት (ዶ/ር) ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ