የካቲት 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ለዩክሬን ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ከሆነ "ስልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን የሚለቁት በምላሹ ዩክሬን የኔቶ አባል የምትሆበት ዕድል ካገኘች ብቻ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ዘለንስኪ ይህን ያሉት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ጦርነት የጀመረችበትን የሦስት ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ፤ ትናንት እሁድ በኪየቭ ለጋዜጠኞች መግለጫ ላይ ነው፡፡

በመግለጫው ላይ ለዩክሬን ሰላም የሚያረጋግጥ ከሆነ ለስልጣን መልቀቅ ዝግጁ ስለመሆናቸው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፤ "ለዩክሬን ሰላም የሚያረጋግጥ ከሆነና ሥራ እንድለቅ ከፈለጉ ዝግጁ ነኝ። ስልጣኔን በኔቶ አባልነት ልለውጠው እችላለሁ።" ብለዋል፡፡

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስትር ፔት ሄግሰት "የኪየቭ ኔቶን የመቀላቀል ጉዳይ የማይሆን ነገር ነው" ያሉ ሲሆን፤ ዩክሬን ይህን ጥረት እንድትተው እንዲሁም፤ የተያዙባትን ግዛቶች የመመለስ ተስፋዋን እንድታቆም ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፤ ማንኛውም የሰላም ድርድርና ስምምነት የሚኖረው ዩክሬን ኔቶን የመቀላቀል እቅዷን ከተወች መሆኑንተናግረዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዝዳንት የእሁድ ዕለቱ ስልጣን የመልቀቅ ሃሳብ ያነሱት፤ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በቀጠለው ፍጥጫ፤ ትራምፕ ዘሌንስኪን ምርጫ ባለማካሄዳቸው "አምባገነን" ሲሉ መጥራታቸውን ተከትሎ ነው።

ዘሌንስኪ በትናንቱ መግለጫቸው በዚህ የትራምፕ አስተያየት "እምብዛምም አልተናደድኩም" የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ "ትኩረቴ አሁናዊ የዩክሬን ሰላምና ደህንነት ላይ እንጂ የሚቀጥሉት 20 ዓመታት አይደለም፤ እኔም በስልጣን ላይ ለአስርት ዓመታት የመቆየት ፍላጎቱም የለኝም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዘሌንስኪ በመግለጫቸው በጦርነቱ ወቅት አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችውን የ500 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ፤ ከማዕድን ክምችቷ እንድትከፍላት ያሳየቸውን የድርድር ፍላጎት የተቃወሙት ሲሆን፤ "500 ቢሊየን ዶላር እውቅና አልሰጥም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

"ይህንን የአሜሪካ ጥያቄ ለመመለስ 250 ዓመታት ሊወስድ ይችላል" ያሉት ዜለንስኪ፤ "የዩክሬን አሥር ትውልዶች መመለስ ያለባቸውን ማንኛውንም ነገር መፈረም እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ ከሦስት ዓመታት በፊት መጠነ ሰፊ ወረራ ከጀመረች በኋላ፤ ዩክሬን በማርሻል ሕግ ሥር የምትገኝ ሲሆን፤ የማርሻል ሕጉ በሀገሪቱ ምርጫ ማካሄድን ይከለክላል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ