የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በግማሽ ዓመቱ ከ10 በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮችና የጤና ተቋማት በልማት ምክንያት ካሉበት አካባቢ በመነሳታቸው እንዲሁም የፍቃድ ዕድሳት ባለማድረጋቸው ምክንያት፤ ወደ ሥራ አለመመለሳቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
"በግማሽ ዓመቱ ምን ያህል የጤና ተቋማት ፍቃዳቸውን ዕድሳት አድርገዋል? ከጥራት ልኬት ጋር በተገናኘ የቁጥጥር ሂደቱ ምን ይመስላል?" ሲል አሐዱ ባለስልጣኑን ጠይቋል።
የባለስልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር ቡድን መሪ ጉሽ አረፋ በሰጡት ምላሽ፤ በከተማዋ ከሚገኙ 182 ተቋማት ውስጥ 172 የሚሆኑት ብቻ የብቃት መለኪያ መስፍርቱን አሟልተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ከ10 በላይ የሚሆኑት ከልማት ጋር ተያይዞ ተቋማቸው በመፍረሱ፣ መለኪያውን ባለሟሟላታቸው እንዲሁም ከገበያ በመውጣታቸው ምክንያት እድሳት አለማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዕድሳት ካላደረጉት የጤና ተቋማት መካከል መሟላት ያሉባቸው መስፈርቶችን አሟልተው የሚመለሱ ተቋማት ድጋሚ ልኬት ተደርጎላቸው ወደ ገበያው እንደሚመለሱም ጠቁመዋል።
በዚህም ሳቢያ በአካባቢዉ የሚገኙ ነዋሪዎች ከመሠረታዊ እስከ ከፍተኛ የጤና አገልግሎቶች እንዳያገኙ እንቅፋት ሊፈጠሩ እንደሚችል ገልጸዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የጤና እና ጤና ነክ አገልግሎት ሙያዊ ብቃት እና ሥነ-ምግባር ባላቸው የጤና ባለሙያዎች ህብረተሰቡ እንዲገለገል እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
በተጨማሪም "የጤና ባለሙያዎችን ብቃት በመመዘን፣ በትብብር በመስራት እንዲሁም ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ ላይ በአጽንኦት እየተሰራ ነው" ሲሉ አብራርተዋል፡፡
"ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ ከፍተኛ ቅንጅታዊ ርብርብ ይደረጋል" ብለዋል።
ቡድን መሪው አክለውም፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ የቁጥጥር ሥራዎችን በማዘመን ችግሮችን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ከ10 በላይ ሆስፒታሎች በልማት በመፍረሳቸውና ፍቃድ ባለማደሳቸው ምክንያት ወደ ሥራ አልተመለሱም ተባለ
