የካቲት 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር የነበረው የአንዲት ግለሰብ የአየር መንገድ ግቢ ውስጥ የልደት ምስል ቀረጻ ከተቋሙ እውቅና ውጭ የተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ አንዲት ግለሰብ በአውሮፕላኑ መወጣጫ ደረጃ ላይ የተለያዩ ዲኮሮችን በማድረግ የተነሳችው ፎቶ ሲዘዋወር መታየቱን ገልጿል፡፡
ግለሰቧ የተነሳችው ለጥገና በቆመ አውሮፕላን ላይ መሆኑን የጠቆመው አየር መንገዱ፤ ድርጊቱ ከተቋሙ እውቅና ውጭ የተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ የሙያ አገልግሎት ሥነ-ምግባርን በመጠበቅ ደረጃውን የሚመጥን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ተቋሙ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጪ ገንዘብ በመቀበል ለግለሰቧ ፈቃድ እንደሰጠ በማስመሰል በተሰራጨው መረጃ ማዘኑን አንስቷል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ÷ ድርጊቱን በፈፀሙ አካላት ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል፡፡

ከሰሞኑ አንዲት ግለሰብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማን የያዘ አውሮፕላን መወጣጫ ደረጃ ላይ የተለያዩ ዲኮሮችን በማድረግ፤ የተለያዩ የልደት ፎቶዎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መልቀቀቋን ተከትሎ፤ ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
አየር መንገዱ ይህን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫው፤ " ድርጊቱ ከእኔ እውቅና ውጪ ነው" ይበል እንጂ፤ እንዴት ይህ ድርጊት እንደተፈጸመና ድርጊቱ ሲፈጸም የአየር መንገዱ ሰራተኞች እና ኃላፊዎች የት እንደነበሩ በግልጽ ይፋ አላደረገም፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ