የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 426 የሚደርሱ የጤና ኬላዎች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በግማሽ ዓመቱ 211 የሚደርሱት ተቋማት በጸጥታ ችግር ምክንያት መውደማቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

አሐዱም "በአጠቃላይ በክልሉ የሚፈጠሩ ግጭቶች በጤናው ዘርፍ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምን ያህል ነው?" ሲል የክልሉን የሕጻናት፣ እናቶች እና ወጣቶች ጤና ቢሮ ጠይቋል፡፡

የቢሮ ዳይሬክተር አብደል ፈታህ በርሄ በሰጡት ምላሽ፤ "በክልሉ ላለፉት አምስት ስድስት ዓመታት የተፈጠሩ ግጭቶች በጤና ዘርፍ ላይ ቀላል የማይባል ውድመት አስከትለዋል" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በክልሉ ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማስፈን ተግዳሮት በመሆኑ ምክንያት፤ በጤናው ኬላዎች ላይ ያስከተለውን ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ በመሆኑ ደግሞ ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑት እናቶችና ሕጻናት እንደሆኑ ያስረዱት ዳይሬክተሩ፤ "በዚህም በግማሽ ዓመቱ እንኳን 140 የሚደርሱ ሰዎች በቂ የሆነ የህክምና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አልፏል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ በአሁኑ ወቅት የወባ በሽታ ስርጭት እና የኮሌራ ወርርሽኝ ስጋት መደቀኑን የተናገሩት አቶ አብደልፈታህ፤ በዚህም በኮሌራ ወረርሽኝ ብቻ በግማሽ ዓመቱ 900 የሚጠጉ ሰዎች መያዛቸውን ገልጸው፤ "በወረርሽኙ የሚሞቱ ሰዎች መጠንም ሦስት በመቶ ደርሷል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ