የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ18 ሺሕ በላይ በችግር ውስጥ የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ መጡበት እንድመለሱ መደረጉን የአዲስ አበባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡
በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጎዳና ላይ የወደቁ ዜጎች ሕጻናትን ጨምሮ በግማሽ ዓመቱ ብቻ ከ18 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደመጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ መደረጉን ለአሐዱ የገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ የማህበራዊ ሴፍትኔት እና ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ግርማ ናቸው፡፡
አቶ ቢኒያም ከ18 ሺሕ ዜጎች ውስጥ ስድስት ሺሕ የሚሆኑት ሕጻናት መሆናቸውን ገልጸው፤ በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕጻናትን ወደ መጠለያ ቦታ እንዲገቡ በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ምግብና ልብስ እንድሁም የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ችግር ምክንያት ጎዳና ላይ የወጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆኑ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በጎዳና ላይ ኑሯቸዉን ያደረጉና እና በተለያዩ ችግር ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደ ማገገሚያ ማዕከል እንዲገቡ በማድረግ እየተሰራ ቢሆንም፤ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ያለ ማዕከል 1 ብቻ በመሆኑ ሁሉንም ለማስገባት ችግር ማጋጠሙንም አብራርተዋል፡፡
ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሕጻናትን ወደ መጡበት ለመመለስ ክልልሎች ፈቃደኛና ለመቀበል ዝግጁ ባለመሆናቸው ተመልሰው ወደ ችግር ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ከዚህ በፊት መገለጹ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ከ18 ሺሕ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉ ተገለጸ
