የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2ኛው ዙር እየለሙ ካሉት የኮሪደር ልማት መስመሮች መካከል አንዱ የሆነው የሰሚት-ፔፕሲ- ጎሮ እስከ ቦሌ መንገድ ከየካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሳምንታት ለትራፊክ እንቅስቃሴ ዝግ እንደሚሆን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ መስመሩ ለትራፊክ ዝግ እንዲሆን የተፈለገው ሥራውን በፍጥነት በመጨረስ መንገዱን ለተጠቃሚው ክፍት ለማድረግ እንዲቻል ታስቦ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በመሆኑም መንገዱ ተጠቃሚዎች ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከፔፕሲ - ጎሮ እና ከጎሮ - ፔፕሲ መንገድ በሁለቱም እቅጣጫ መንገዱ የሚዘጋ በመሆኑ፤ ከፒፕሲ ወደ ጎሮ የሚጓዙ አሽከርከሪዎች በጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ወደ ኢንዱስትሪ መንደር ቦሌ ወረዳ 11 በኩል ጎሮ የሚያገናኘውን መንገድ እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡
ከጎሮ ወደ ፒፕሲ የሚመለሱ ተጓዦች ደግሞ በጃክሮስ - ፊጋ- ሰሀሊተ ምህረት ወደ ዋና መስመር በመግባት መጠቀም እንደሚችሉም ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪ ሌሎች አማራጭ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡
ተገልጋዮች የመንገዱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ለሚያሳዩት ትብብርም ባለስልጣኑ ከወዲሁ ምስጋና ማቅረቡን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ከሰሚት-ፔፕሲ- ጎሮ እስከ ቦሌ ያለው መንገድ በሁለቱም አቅጣጫ ለሳምንታት እንደሚዘጋ ተገለጸ
