የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) እርዳታ ማቆም በትግራይ ክልል ተፈናቅለው የሚገኙ 1 ሚሊዮን ገደማ ተፈናቃዮችን ችግር ላይ የሚጥል ውሳኔ መሆኑን ፅላል ምዕራብ ትግራይ የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ለአሐዱ ገልጿል፡፡

የድርጅቱ ፕሬዘዳንት አቶ ፀጋይ ተጠምቀ፤ "ድርጅቱ እርዳታ ማቆሙ ተከትሎ በተፈናቃይ ዜጎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም" ብለዋል፡፡

Post image

ይህ ጉዳይ በተለይ ተፈናቃዮችን ለስደት ሲብስም ደግሞ የፀጥታ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን በመረዳት፤ ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ጨምሮ ለተለያዩ የውጭ ሀገር ረጂ ተቋማት እንዲሁም ለፌደራል መንግሥት እና ለጊዜያዊ አስተዳዳደሩ እርዳታ መቆሙ ተገቢ ውሳኔ አለመሆኑን በመጥቀስ ደብዳቤ መፃፋቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

"የፌደራል መንግሥትም ሆነ የጊዚያዊ አስተዳደሩ ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ ሲቻል ብቻ በመሆኑ፤ ይህንን ሊያደርጉ ይገባል" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡

ከአራት ዓመታት በላይ በመጠለያ ጣቢያ ኑሯቸውን ያደረጉት ተፈናቃይ በበኩላቸው "የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ውሳኔ ስጋት እንደፈጠረባቸው በመግለጽ፤ "የፌደራል መንግሥትም ሆነ ጊዜዊ አስተዳሩ ወደ ቀያችን ይመልሱን" ብለዋል፡፡

ከአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ በተጨማሪ የህወሓት የውስጥ ክፍፍል በትግራይ ላይ የፈጠረው ችግር ይበልጥ ስጋታቸውን እንደጨመረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ሕብረት በክልሉ የተፈጠረውን የእርዳታ እህል ለማጣራት በማሰብ እርዳታ ያቆመበት ሁኔታን የሚያስታውሱት የፅላል ምዕራብ ትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ፕሬዝዳንት ፀጋይ ተጠምቀ፤ "ይህ ሁኔታ ተፈናቃዮች ባሉበት በዚህ ሁኔታ እርዳታ ማቆም ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እንደ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትም በዋናነት የፕሪቶሪያው ውል ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር የሚያስችል ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ 'ይበቃል' የሚለው ንቅናቄ የዚህ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

"በመሆኑም እርዳታው በዚሁ የሚቆም ከሆነ የከፋ አደጋ የሚፈጥር በመሆኑ፤ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ አሳውቀናል" ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ