ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በያዝነው የበጀት ዓመት ባለፉት 6 ወራት ውስጥ በተካሄደ ድንገተኛ ክትትል ያለ ደረሰኝ ሽያጭ ሲያካሂዱ በተገኙ 4 ሺሕ 696 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡

የተቋሙ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ፤ "ሕጋዊ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ሽያጭ ባከናወኑ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም የገንዘብ መቀጮ ተጥሎባቸዋል" ብለዋል፡፡

ተቋሙ ጥፋተኞች ላይ ከጣለው አስተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ ጉዳያቸው በሕግ የተያዘ የንግድ ተቋማት ስለመኖራቸውም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ድንገተኛ ክትትል በማድረግ ያለ ደረሰኝ በሚሸጡ 671 የሚደርሱ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል 632 በሚሆኑት የገንዘብ መቀጮ የተቀጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በቅጣቱ የተገኘ ገንዘብ 63 ሚሊዮን 200 ብር መሰብሰቡንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

"በደረጃ ሐ እና ለ ግብር ከፋይነት ከተመዘገቡት ነጋዴዎች መካከል ደግሞ፤ 3 ሺሕ 225 የንግድ ተቋማት ያለ ደረሰን ግብይት በመፈጸማቸው ለገንዘብ ቅጣት ተዳርገዋል" ብለዋል።

በአጠቃላይ በ6 ወር ውስጥ 297 ሚሊዮን ብር በተለያዩ የቅጣት ዓይነቶች መሰብሰቡን ቢሮው አስታውቀዋል።

እንዲሁም ንብረት በማዘዋወር፣ ደረሰኝ ሳይቆርጡ በመሸጥ፣ እና በመሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶች የተጠረጠሩ 839 የንግድ ተቋማት ደግሞ ጉዳያቸው በሕግ እየታየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ያለ ደረሰኝ ግብይትን ለማስቆም እንዲሁም የሕግ ተገዥነትን ለማስፈን ከባለ ድርሻ አካላት በጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ