ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጤና ተቋማት ላይ በወቅቱ መገዛትና መሟላት ያለባቸውን የሕክምና ግብዓትና መድኃኒት ለማሟላት በበጀት እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በጤና ተቋማት ላይ የሕክምና ግብዓት እና የመድኃኒት እጥረት የሚስተዋበትን ምክንያት በተመለከተ ምልከታ መከናወኑን ያነሱት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ፤ በሂደቱም በጤና ተቋማት ላይ ለመድኃኒትና ለሕክምና ግብዓት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ግዢ ለመፈጸም በበጀት እጥረት ምክንያት አስቻይ ሁኔታ አለመፈጠሩን ለመመልከት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለውም፤ የሕክምና ግብዓትን በጤና ተቋማት ላይ በበቂ ሁኔታ እንዲገኙ የበጀት እጥረት በመኖሩ ምክንያት አንዳንድ መድኃኒቶች በአስገዳጅነት በሀገር ውስጥ ምርት እንዲከናወኑ ስለመደረጉ ተናግረዋል፡፡

በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር እንዲሁም በበዜጎች የሚነሱ ቅሬታዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም በጤና ተቋማት ላይ የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓትን በበቂ ሁኔታ እንዲገኙ ለማስቻል 13 የሚሆኑ የመንግሥት ተቋማትን ያካተተ ፎርም መቋቋሙን ሚኒስትር ዲኤታዋ አስታውቀዋል፡፡

አክለውም፤ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ለሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልጉ መድኃት እና የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ማምረት እንደ መፍትሄ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በጤና ተቋማት ላይ የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓትን በበቂ ሁኔታ አለመኖር በህክምና አገልግሎት ላይ የሚያሳድረው ጫና ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ መሰል ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ