ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ አሁን እየተስተዋለ ያለውን ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች መነሻ በማድረግ በሀይማኖት አባቶች ሀገራዊ የሰላም ጥሪና የጸሎት መርሃ ግብር ተካሂዷል።

"በተለይም አሁንም ድረስ በአንድ አንድ የኢትዮያ ክፍሎች ያለው አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት እንዲሁም ክፉ የወንጀል ድርጊቶች ለሀገራችን የሚመጥኑ አይደሉም" ያሉት የሀይማኖት አባቶች፤ "በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ባለመድረሳችን ሰላም እየደፈረሰ፣ የሀይማኖት ልዕልና እየላላ መጥቷል" ብለዋል።

Post image


"በዚህም ምክንያት የሰላማዊ ሰዎች መጎዳት፣ የአንድነት መሻከር፣ በድርቅ መመታት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ለጎርፍ እና ለመሬታ ናዳ እየተጋለጥን ለሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች እየተጋለጥን እንገኛለን" ሲሉ ገልጸዋል።

በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የጸሎት መርሃ ግብር ያካሄዱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን ጨምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዲሁም፤ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የፕሮቴስታንት እምነት አባቶች ተገኝተው በሰላም ጉዳይ የጸሎት መርሃ ግብር አከናውነዋል።

Post image

"የሀይማኖት መሪዎቹ በርካታ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ቢኖሩንም በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም ሰላምን ለሀገራችን ማምጣት አልቻልንም" ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰላምን ለማጽናት የሀይማኖት አባቶች፣ የፖለቲከኞች፣ የመሪዎች እንዲሁም የሁሉም ማኅበረሰብ ሚና ከፍተኛ ነዉ ተብሏል።

Post imagePost image

የኢትዮጵያ የሲቪል እና የሙያ ማህበራት ምክር ቤት የተለያዩ የሲቪል እና ሙያ ማህበራትን ፌዴሬሽኖችን፣ ኮንፌዴሬሽኖችን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሕዝባዊ ማህበራትን እና የሀይማኖት ተቋማትን ያቀፈ ምክር ቤት ሲሆን፤ በውስጡ 51 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባላትን አቅፎ የያዘ ተቋም መሆኑ ተገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ