የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ወይንም ግሎባል አልያንስ የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም፤ በሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ ለድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ ከ115 ሺሕ በላይ ዜጎች ሦስት ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

Post image

ድርጅቱ በወረዳው ውስጥ ድርቁ በጸናባቸው አምስት ቀበሌዎች በመገኘት ምልከታ ማድረጉን የገለጹት የድርጅቱ የአዲስ አበባ ተወካይ በፍቃዱ አባይ፤ በእነዚህ ቀበሌዎች ላይ ብቻ ከ115 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ተወካዩ በተመረጡት አምስት ቀበሌዎች ላሚገኙ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፉ መደረጉን አንስተው፤ ድርጅቱ ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር 778 ኩንታል የበቆሎ እህል ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

Post image

ቡግና ወረዳ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ መከሰቱን የገለጸው ድርጅቱ፤ በተለይም በተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመዝቡ እና የሚዘንበው ደግሞ በረዶ የቀላቀለ በመሆኑ ሰብሎች እያጠፋባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ከዛም ባሸገር የተምች ወረርሽኝ እና የጸጥታ ችግር መኖሩን በመግለጽ፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመሆን እርዳታውን ማድረስ መቻሉንም ገልጿል፡፡

አከባቢው ላይ ያለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ የመሠረተ ልማት ችግር መኖሩን በማንሳት፤ ሁኔታው የከፋ መሆኑን አቶ በፍቃዱ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image

በአካባቢው ማዳሪያ ከገባ ሁለት ዓመት በመሆኑ ምርት ማምረት አለመቻላቸውን በመግለጽም፤ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል፡፡

ድርጀቱም በቀጣይ የአካባባው ጸጥታ ሁኔታ የሚሻሻል ከሆነ፤ ተጨማሪ ድጋፎች ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውም የግሎባል አልያንስ የኢትዮጵያ ተወካይ ገልጸዋል፡፡

የቡግና ወረዳ በተከተሰተ ድርቅ ሳቢያ በርካቶች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ወደ ወረዳው በቂ እርዳታ እየገባ አለመሆኑን አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ