የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዓ.ም 6 ወራት ውስጥ 125 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 111 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን አስታውቋል፡፡

በዚህም የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጿል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ምክር ቤቱ በጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላት የ2017 የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።

በግምገማው ላይም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የገቢ አሰባሰባችን አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው 74 ነጠብ 3 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር፤ በ37 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር (50 በመቶ) ምርታዊ እድገት አሳይቷል" ብለዋል፡፡

ባለፉት 6 ወራት የከተማ አስተዳደሩን ሀብት አመዳደብና አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማሳደግ የበጀት ድልድል የከተማ አስተዳዳሩን የትኩረት አቅጣጫዎች በመለየት ለዘላቂ ልማት ዘርፎች እንዲደለደል መደረጉንም ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ለዘላቂ ልማት የሚመደበውን የመንግሥት በጀት በ2016 ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 71 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ አፈፃፀሙ 71 በመቶ መድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

ይህም ለመደበኛ 29 ቢሊዮን 49 ሚሊዮን 654 ሺሕ 788 ብር እንዲሁም ለካፒታል ብር ብር 64 ቢሊዮን 188 ሚሊዮን 241 ሺሕ 80 ብር በድምሩ 93 ቢሊዮን 237 ሚሊዮን 895 ሺሕ 868 ብር (98 ነጠብ 34 በመቶ) ክፍያ መፈፀም መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አፈፃፀሙም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጠቅላላ 66 ቢሊዮን 65 ሚሊዮን 700 ሺሕ 754 ብር ጋር ሲነፃፀር፤ የ27 ቢሊዮን 172 ሚሊዮን 195 ሺሕ 114 ብር ወይንም 41 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አስረድተዋል።

Post image

የተጨማሪ እሴት ታክስ ስርዓት ውስጥ መግባት እየተገባቸው ያልገቡትን 8 ሺሕ 450 የንግድ ተቋማትን ወደ ቫት ስርዓት እንዲገቡ በመደረጉና የታክስ ኦዲትና ሽፋንና ውጤታማነት ለማሻሻልና ለማስፋት በተሰራው ሥራ፣ ባሻገር በመርካቶና በከተማችን በሚገኙ ትልልቅ የንግድ ቦታዎች የተሰራው የቁጥጥርና ሕግ የማስከበር ሥራ ገቢ ከማሳደግ ባሻገር ፍትሃዊነት እንዲሰፍን አስተዋፅኦ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከተማ አሰተዳደሩ ባለፉት 6 ወራት በጤናው ዘርፍ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ከንቲባዋ ያብራሩ ሲሆን፤ ከእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት አኳያ የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት 94 ሺሕ 812 እቅድ ተያዞ 94 ሺሕ 548 ለሚሆኑ እናቶች አገልግሎት በመስጠት የዕቅዱን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም አምና ከነበረው 2 ነጥብ 3 ሚሊየን አጠቃላይ በፕሮግራሙ የታቀፉ አባላት ቁጥር ዘንድሮ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነትንም ለ1 ሚሊዮን 330 ሺሕ 562 በማድረስ ተደራሽና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡

የጤና መረጃ ስርዓትን ከማዘመንና ዲጂታል ከማድረግ ረገድም የጤና መረጃ ስርዓታቸውን በሙሉ ወረቀት አልባ ካደረጉ 40 ጤና ተቋማት ወደ 91 ጤና ተቋማት በማሳደግ እቅዱን ማሳካት መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት አመላካች መለኪያዎችን በኩል፤ የአስተኝቶ ሕክምና ታካሚዎች ሞት ምጣኔ በእቅድ የተያዘው 1 ነጥብ 4 በመቶ እና ከዛ በታች ማድረስ ሲሆን፤ 1 ነጠብ 2 በመቶ በማከናወን እቅዱን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተሰጠው የሕክምና አገልግሎት ጥራት አመላካቾችም የዓለም የጤና ድርጅት በማደግ ላይ ላሉ ሃገራት ያወጣውን ስታንዳርድም ሆነ ሀገራዊ ኢላማ በሚገባ ማሳካት የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ አበባ በአፍሪካ ሕጻናት ዕድገት ምቹ እንድትሆን ለማስቻል በቀዳማይ የልጅነት ፕሮግራም በ 3 ዓመት ለ1000 ሕጻናት ማቆያ ለማቋቋም በዕቅድ ተይዞ፤ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ 822 የተዘጋጀ ሲሆን፤ በዚሕም ከ10 ሺሕ በላይ ሕጻናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም ከ 11 ሺሕ 900 ነፍሰ-ጡር ሴቶች፣ አጥቢ እናቶችና ሕፃናት የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም፤ ለሰንበት ዝግ በሚደረጉ መንገዶች በርካታ ሕጻናት የመጫወቻ ስፍራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን በሪፖርታቸው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ለ7 ሺሕ 591 አረጋውያን እና ለ1 ሺሕ 605 አካል ጉዳተኞች መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የስነልቦና፣ የማህበራዊ እና የተሃድሶ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤ ለ582 አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍም እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም 1 ሺሕ 314 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማልማትና ማስፋት ለ10 ሚሊዮን 957 ሺሕ 268 የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን መናገራቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው በሪፖርቱ ላይ ከተወያየ በኋላ የተለያዩ አዋጆችን መርምር ይፀድቃል ተብሎም ይጠበቃ፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ